(ኢሳት ዲሲ–ታህሳስ 8/2011) በኢትዮጵያ ውስጥ ሕገ-መንግስት መጣስም ሆነ በክልሎች ጣልቃ መግባት ዛሬ የተጀመረ አይደለም ሲሉ ሌተናል ጀኔራል ጻድቃን ገብረተንሳይ ገለጹ።
ከአንድ አካባቢ የመጡ ሰዎች የፖለቲካስልጣኑን በበላይነት ይዘው ሕገ-መንግስቱን እየጣሱ ሕግ ሳይገዛቸው የቆዩበት ሁኔታ ዛሬ ለተከሰተው ችግር አስተዋጽኦ ማድረጉንምጄኔራሉ አመልክተዋል።
የሕዉሃት ነባር ታጋይ እና በኢህአዴግ የስልጣን ዘመን እስከ ግንቦት ወር 1993 የኢትዮጵያ ጦር ሃይሎች ጠቅላይ ኤታማጆር ሹም የነበሩት ሌተናል ጄኔራል ጻድቃን ገብረተንሳይ ከትግራይ ክልል ቴሌቪዥን ጋር ባደረጉት ቃለ-ምልልስ የፌደራል መንግስቱም ሆነ የክልል መንግስታት ከእልህ እንዲወጡም ጥሪ አቅርበዋል።
ዛሬ በኢትዮጵያ የተከሰተው ቀውስ አንድ ሂደቱ ሽግግር ላይ በመሆኑ በሌላም በኩል መንግስት ፍኖተ ካርታ አለማስቀመጡ እንዲሁም የተቃዋሚዎች አለጠናከር ለችግሩ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው አመልክተዋል።
ሕገ-መንግስቱ እየተጣሰ ነው በሚል ከትግራይ ክልል ቴሌቭዥን ጥያቄ የቀረበላቸው ሌተናል ጄኔራል ጻድቃን ገብረተንሳይ ሕገ-መንግስት መጣስም ሆነ በክልሎች ጣልቃ መግባት ዛሬ የተጀመረ ሳይሆን የነበረ ስህተት ነው ብለዋል።
አሁን ስልጣን ላይ ያለው መንግስት ግን ስህተትን በስህተት ከማረም እንዲታቀብም ጥሪ አቅርበዋል።
በኢትዮጵያ ያለው ሕገ-መንግስት ማንነትን መሰረት ያደረገ ነው ያሉት ጻድቃን ገብረተንሳይ በዚህ ሁኔታ ከአንድ አካባቢ የመጡ ሰዎች ወሳኙን የፖለቲካ ስልጣን ይዘው ሕገ-መንግስቱን እየጣሱ ከህግ በላይ ሆነው መቀጠላቸው ሌላው አካባቢ ይህንን አልቀበልም ማለቱ የሚጠበቅ እንደነበረም አመልክተዋል። ሕገ-መንግስቱን ማክበር የግድ መሆኑንም አስረድተዋል።
ከማንነት ጋር በተያያዘ የተነሱ ጥያቄዎችን ለግዜውም ቢሆን ማዘግየቱ ይጠቅማል በማለት የመከሩት ጻድቃን ገብረተንሳይ አጣዳፊ ነው የሚባል ከሆነ ግን በሕገ-መንግስቱ መሰረት እንዲፈታ ጥሪ አቅርበዋል።
ግዜው የኔ ነው በሚል የጉልበት አማራጭ ከተወሰደ ሌላውም በጉልበት ልመክት ሲል ችግር ይፈጥራል ብለዋል።
የመከላከያ ሰራዊትን በተመለከተ ችግሮች ባለባቸው አካባቢዎች መሰማራቱ ተገቢ ነው ያሉት ሌተናል ጄኔራል ጻድቃን ገብረተንሳይ አገባቡ ግን በሕገ-መንግስቱ በተቀመጠው ስልጣን መሰረት መሆን እንዳለበትም ጨምረው ገልጸዋል።
አሁን እንዴት እንደገባ ግን መረጃው እንደሌላቸው ገልጸዋል።