በኮንጎ ዴሞክራቲክ የሚካሄደው ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ከፍተኛ ውጥረት አነገሰ

(ኢሳት ዲሲ–ታህሳስ 8/2011)በኮንጎ ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ በመጪው ዕሁድ የሚካሄደው ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ በሃገሪቱ ከፍተኛ ውጥረት መፍጠሩ ተሰማ።

አሜሪካ ዜጎቿ ከርዕሰ መዲናዋኪንሻሳና ሌሎች ከተሞች ለቀው እንዲወጡ ያሳሰበች ሲሆን ብሪታኒያ ዜጎቿ ወደ ኮንጎ ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ እንዳይገቡ ማስጠንቀቂያሰጥታለች።

ላለፉት 17 ዓመታት በመሪነት የቆዩትን ፕሬዝዳንት ጆሴፍ ካቢላን ለመተካት እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር ከፊታችን እሁድ ታህሳስ 23 የሚካሄደው ምርጫ በሰላም እንዲጠናቀቅ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ለተቀናቃኝ ወገኖች ጥሪ አቅርቧል።

ከ30 ዓመታት በላይ የቀድሞዋን ዛየር የአሁኗን ኮንጎ ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክን የመሩት ሞቡቱ ሴሴ ሴኮ በሎራን ካቢላ በተመሩ ሽምቅ ውጊያ ተሸንፈው ወደ ሞሮኮ ሲሰደዱ ሎራን ካቢላ እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር ግንቦት 16/1997 የዛየርን የመሪነት ስልጣን ጨበጡ።

የሃገሪቱንም ስያሜ ከዛየር ወደ ኮንጎ ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ለወጡ።

ከአራት ዓመት በኋላ ሎራን ካቢላ በራሳቸው ጠባቂ እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር  ጥር 16/2001 ሲገደሉ ልጃቸው ጆሴፍ ካቢላ የመሪነቱን ስልጣን ተረከቡ።

እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር ከጥር 16/2001 ጀምሮ የዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ መሪነትን የያዙት ጆሴፍ ካቢላ በሕግ በተቀመጠው መሰረት የስልጣን ዘመናቸው ከሁለት አመት በፊት እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር ታህሳስ 20/2016 ያበቃ ቢሆንም በስልጣን ለመቀጠል ባላቸው ፍላጎት በተቀሰቀሰ አመጽ 47 ያህል ሰዎች ተገድለዋል።

በሕዝባዊው ተቃውሞና በአለም አቀፉ ማህበረሰብ ግፊት የፊታችን እሁድ በሚደረግ ምርጫ ጆሴፍ ካቢላ ስልጣናቸውን ለመልቀቅ ተስማምተዋል።

የምርጫ ዝግጅቱ መቀጠሉም ተሰምቷል።

ሆኖም ሰላማዊ የነበረው ሒደት ባለፈው ሳምንት ችግር እየገጠመው ይገኛል።

በተቃዋሚዎች የምርጫ ዘመቻ ላይ በተከፈተ ተኩስ 4 ሰዎች ሲገደሉ የምርጫ ማሽኖችና የድምጽ መስጫ ሳጥኖች ኪንሻሳ ላይ የእሳት ቃጠሎ እንደደረሰባቸው ታውቋል።

ይህም በሃገሪቱ ከምርጫው አንድ ሳምንት ቀደም ብሎ ውጥረት አስከትሏል።

አሜሪካ ከአደጋ ጊዜ ሰራተኞች ውጭ ሙሉ ዜጎቿና ቤተሰቦቻቸው ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎን እንዲለቁ ባለፈው ቅዳሜ ማሳሰቢያ ሰታለች።

ብርታኒያ ደግሞ ረቡዕ ዕለት ዜጎቿ ወደዚያ እንዳይሔዱ ማስጠንቀቂያ ሰጥታለች።

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ተቀናቃኝ ሃይሎች ሒደቱ በሰላም እንዲጠናቀቅ አስፈላጊውን ነገር ሁሉ ያደርጉ ዘንድ ማሳሰቢያ ሰጥቷል።