የተቃውሞ ሰልፍ በአዲስ አበባ ተጠራ

(ኢሳት ዲሲ–በታህሳስ 3/2011) በኢትዮጵያ የሚካሄደውን ለውጥ ለማደናቀፍ የተለያዩ ግጭቶችን እየፈጠሩ ያሉ አካላትን የሚያወግዝ የተቃውሞ ሰልፍ በአዲስ አበባ ተጠራ።

የፊታችን እሁድ የሚካሄደውን ሰልፍየአዲስ አበባ መስተዳድር እውቅና እንዲሰጠው አስተባባሪዎቹ ጥያቄ ያቀረቡ ቢሆንም መስተዳድሩ ግን እውቅና እንዳልሰጠው አስታውቋል።

ፋይል 

የታቀደው ሰልፍ በኢትዮጵያውያን የህሊና እስረኞች ላይ በህወሃት አገዛዝ ሰቆቃ የፈጸሙ ግለሰቦች ለፍርድ እንዲቀርቡ ይጠይቃል ተብሎ ይጠበቃል።

በሃገሪቱ በተለያዩ አካባቢዎች የተከሰቱት መፈናቀሎች እንዲቆሙና የለውጡን ሂደት የሚያደናቅፉ ሃይሎች ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡ የሚያሳስብ የተቃውሞ ሰልፍ እንደሚሆን ከአስተባባሪዎቹ የተገኘው መረጃ ያመልክታል።

በትላንትናው ዕለት በመንግስት የተለያዩ የመገናኛ ብዙሃን የቀረበውና በማዕከላዊና በአንዳንድ ስውር እስር ቤቶች የተፈጸሙትን ሰቆቃዎች የሚያሳየው ዘጋቢ ፊልም ከየአቅጣጫው ቁጣን ቀስቅሷል።

ለእሁድ የተጠራውን ሰልፍ የሚያስተባብረው ኮሚቴ ለኢሳት እንደገለጸው በኢትዮጵያውያን ላይ የጭካኔ ርምጃ ሲወስዱ የነበሩ ሃይሎች ከጥፋት መስመራቸው ላይ ሆነው ሀገሪቱን በተለያዩ ክፍሎች እያመሷት መሆኑ ለሰልፉ መጠራት መክንያት ሆኗል።

የትላንቱ ዘጋቢ ፊልም የሰላማዊ ሰልፉን አስፈላጊነት በሚገባ ያመለከተ በመሆኑ ኢትዮጵያውያን እንዲሳተፉና የለውጥ አደናቃፊዎችን እንዲያወግዙ ጥሪ ተደርጓል።

ባለፈው ቅዳሜ በመቀሌ ትዕይንተ ህዝብ እንዲካሄድ ያደረገውና ከማዕከላዊ መንግስት የተወገደው የህወሃት አገዛዝ በተለያዩ የኢትዮጵያ አካባቢዎች እየተፈጸሙ ላሉ ግጭቶችና መፈናቀሎች ተጠያቂ ነው የሚለው የአዲስ አበባ የተቃውሞ ሰልፍ አስተባባሪ ኮሚቴ እነሱ ለጥፋት አደባባይ ሲወጡ እኛ ለሀገራችን መልካም ተስፋ ሰንቀን ድምጻችንን ማስማት አለብን ብሏል።

በአዲስ አበባ በተጠራው የእሁዱ ሰልፍ ግፍና ስቃይ መከራ የደረሰባቸው ኢትዮጵያውያን ካሳ እንዲሰጣቸው፣ አሰቃቂውን ወንጀል የፈጸሙት ግለሰቦች ከያሉበት ተይዘው ለፍርድ እንዲቀርቡ የሚጠይቁ መልዕክቶች እንደሚተላለፉ አስተባባሪዎቹ ገልጸዋል።

በተለያዩ የኢትዮጵያ አካባቢዎች መፈናቀሉ እንዲቆምና ተፈናቃዮች ወደ ቀዬአቸው እንዲመለሱ መንግስትና ዓለም ዓቀፍ ማህበረሰብ አፋጣኝ ርምጃ እንዲወስዱ በሰልፉ ላይ ይጠየቃል ተብሏል።

ለውጡን የሚያደናቅፉና አሁንም ከመንግስት ጉያ ውስጥ የሚገኙ ባለስልጣናትን አዲሱ አመራር ርምጃ በመውሰድ ራሱን እንዲያጠራ ይጠይቃል የተባለው ሰልፍ ለጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ የለውጥ እንቅስቃሴ በድጋሚ ድጋፉን የሚያሳይ ይሆናል ተብሏል።

ዘግይቶ በደረሰን ዜና ደግሞ የአዲስ አበባ አስተዳደር የእሁዱን ሰልፍ እውቅና ነፍጎታል።

የአዲስ አበባ ፖሊስም በከተማዋ የተጠራው ሰልፍ እውቅና የለውም ሲል አሳስቧል።

ሰልፉን ያዘጋጀው አካል ማንነትና ምንነት የማይታወቅ በመሆኑ ጥበቃ ለማድረግ እቸገራለሁ ያለው ፖሊስ በአዲስ አበባ መስተዳድር ጭምር እውቅና የተነፈገውን ሰልፍ ማካሄድ አይቻልም ብሏል።

አስተባባሪዎቹ ሰልፍ ማድረግ መብትና የሚጠበቅቸው ማሳወቅ ብቻ በመሆኑ ያንን አድርገናል ያሉ ሲሆን በጥበቃው ዙሪያ ተጨማሪ ውይይቶችን ከመስተዳድሩ ጋር ለማድረግ መዘጋጀታቸውን ለኢሳት ገልጸዋል።