ዩ ኤስ አይ ዲ የሚያቀርበውን ድጋፍ ማቋረጡን አስታወቀ

(ኢሳት ዲሲ–ታህሳስ 3/2011) የአሜሪካው የሰብዓዊ እርዳታ ተቋም ዩ ኤስ አይ ዲ በጌዲዮና ጉጂ አካባቢዎች ባገረሸው ውጥረት ምክንያት ለተፈናቃዮች የሚያቀርበውን ድጋፍ ማቋረጡን አስታወቀ።

ካለፈው ሳምንት መጨረሻ አንስቶድርጅቱ የሚሰጠውን ድጋፍ ላልተወሰነ ጊዜ ማቆሙን ያስታወቀው የድርጅቱ ዳይሬክተር በአካባቢዎቹ ቆየተው ከተመለሱ በኋላ ነው።

ፋይል 

የዩኤስ አይዲ ዳይሬክተር ሌስሊ ሪድ ከኢትዮጵያ ብሮድካስት ኮርፖሬሽን ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ በጌዲዮና ጉጂ አካባቢዎች ዳግም የተፈጠረው አለመረጋጋት የድርጅቱን እንቅስቃሴ አስተጓጉሎታል።

በቀርቻ ቡሌ ሆራና ገላና የተቀሰቀሰው ግጭት የተመለሱትን ተፈናቃዮች ዳግም ማፈናቀሉንም ዩ ኤስ አይዲ አስታውቋል።

ከአንድ ዓመት በላይ ዘልቋል። ወደ 1ሚሊየን ገደማ ሰዎችን አፈናቅሏል። ከ300 በላይ የሚሆኑትን ለሞት ዳርጓል። ቤት ፈርሷል። መንደር ተቃጥሏል። የእምነት ተቋማት ጋይተዋል።

የእርሻ ማሳዎች ከነእህላቸው በእሳት ተያይዘው ወድመዋል።

የደረሰው ጥፋት ከፍተኛ ነው። ማንነትን መነሻ አድርጎ በጉጂና በጌዲዮ ማህበረሰቦች መካከል የተፈጠረው ግጭት የሰው ህይወት በማጥፋትና ከፍተኛ ሃብትና ንብረት በማውደም የሚቆም አልሆነም።

ከአካባቢያችን ልቀቁ በሚል የተጀመረውን ጥቃት ሽሽት በኢትዮጵያ ታሪክ ሁለተኛ የተባለውን የሰዎች መፈናቀል አስከትሏል።

በሶማሌና ኦሮሚያ ክልሎች መካከል በተፈጠረ ግጭት ከተፈናቀለው ዜጋ ቁጥር ቀጥሎ በሁለተኛ ደረጃ የተመዘገበው የሰዎች መፈናቀል የተከሰተው በጊዲዮና ጉጂ ማህብረሰቦች መካከል በተፈጠረው ግጭት ነው። 

ይህን ሰብዓዊ ቀውስ ለመታደግ በመንግስት ከሚደረገው እንቅስቃሴ በተጨማሪ በዓለም ዓቀፍ የግብረሰናይ ተቋማት የእርዳታ ማቅረብ ስራ መጀመሩ የሚታወስ ነው።

የተፈናቀሉትንና በተለያዩ ትምህርት ቤቶችና የመንግስት ተቋማት ተጠልለው ለሚገኙት ዜጎች አስቸኳይ የሆነ እርዳታ ለማቅረብ ከ20ሚሊየን ዶላር በላይ እንደሚያስፈልግ የገለጸው የአለም አቀፉ የስደተኞች ድርጅት አይ ኦ ኤም ሁኔታው እጅግ አሳሳቢ እንደሆነ በመጥቀስ ዓለም ዓቀፉ ማህበረሰብ እንዲረባረብ የጠየቀው መፈናቀሉ በተከሰተ ሰሞን ነበር።

ምላሽ በመስጠት ወደ ግጭቱ አካባቢ የተሰማራው የአሜሪካው የሰብዓዊ እርዳታ ድርጅት ዩ ኤስ አይ ዲ ባለፉት ሰባት ወራት የእርዳታ እህል ሲያቀርብ ቆይቷል።

ያዝ ለቀቅ ከሚያደርገው የአካባቢው የሰላም ሁኔታ ጋር እርዳታ ማቅረብ አስቸጋሪ የሆነበት ድርጅቱ ሰሞኑን እንቅስቃሴውን ሙሉ በሙሉ ማቋረጡን አስታውቋል።

የዩ ኤስ አይ ዲ ዳይሬክተር ሊዝሊ ሪድ ለኢትዮጵያ ብሮድካስት ኮርፖሬሽን ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ ካለፈው ሳምንት ጀምሮ እንደአዲስ በተቀሰቀሰው ግጭት ምክንያት ድርጅቱ የእርዳታ ማቅረብ ተግባሩን መቀጠል አልቻለም ብለዋል።

ሊዝሊ ሰሞኑን በአካባቢው እንደነበሩ ጠቅሰው አለመረጋጋት ተፈጥሮ የድርጅታቸው ስራ መታወኩን አስታውቀዋል።

በተለይም በቀርቻ፣ ቡሌ ሆራና ገላና በተሰኙ አካባቢዎች ያገረሽው ግጭት እንቅስቃሴያቸውን አስተጓጉሎታል።

ሁኔታው እየተባባሰ መጥቷል ያሉት ዳይሬክተሯ በዚህም ምክንያት የእርዳታ እንቅስቃሴው ላልተወሰነ ጊዜ እንዲቋረጥ መደረጉን ገልጸዋል።

የዩ ኤስ አይዲ ዳይሬክተር ሊዝሊ ሪድ ጨምረው እንደገለጹት ሰሞኑን በተፈጠረው አለመረጋጋት የተነሳ ድርጅቱ ለእርዳታ ያከማቸው እህል ማንነታቸው ባልታወቁ ቡድኖች ተዘርፏል።

800 ተፈናቃዮችን ለአንድ ወር ሊመግብ የሚችል የእርዳታ እህል ከድርጅቱ መጋዘን ተዘርፏል ያሉት ዳይሬክተሯ ይህ ሁኔታ በአካባቢው ስራችንን እንዳንቀጥል አድርጎናል ሲሉ ተናግረዋል።

በድርጅቱ ሰራተኞች ላይም ማስፈራራትና ወከባ ይፈጸማል ብለዋል። ዩ ኤስ አይዲ በቀርቻ ቡሌ ሆራና ገላና ይሰጥ የነበረው ድጋፍ በመቋረጡ 140ሺህ የሚሆኑ ተፈናቃዮች አደጋ ላይ መውደቃቸውን ዳይሬክተሯ ገልጸዋል።

ዘራፊዎቹም ሆኑ በግጭቱ ውስጥ የሚሳተፉ ሃይሎች እየጎዱ ያሉት ዩ ኤስ አይዲን ሳይሆን ተፈናቅሎ በችግር ውስጥ የሚገኘውን የገዛ ወገናቸውን ነው ሲሉ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።