(ኢሳት ዲሲ–ታህሳስ 2/2011)በቅርቡ ከ50 ለሚበልጡ ዲፕሎማቶችተሰጠ ከተባለው ሹመት ጋር ተያይዞ ዝርዝሩ ይፋ ሳይሆን የቀረው ከተሿሚዎቹ ውስጥ ተጠርጣሪ ወንጀለኞች በመገኘታቸው እንደሆነ የውጭጉዳይ ሚኒስቴር ምንጮች ገለጹ።
ለአዲሱ ሹመት ታጭተው ከነበሩት ውስጥ አንዱ በሳምንቱ መጨረሻ በቁጥጥር ስር መዋላቸው ታውቋል።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ በቅርቡ 58 ዲፕሎማቶችና ሰራተኞች መመደቡን በገለጹበት ወቅት ከዝርዝሩ ውስጥ የተጠቀሱት አቶ መአሾ ኪዳኔ በሳምንቱ መጨረሻ በቁጥጥር ስር ውለዋል።
በብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት ከፍተኛ አመራር እንደነበሩ የተጠቀሱት አቶ መአሾ ኪዳኔ ከሌላው የመስሪያ ቤታቸው ባልደረባ አቶ ሐዱሽ ካሳ ጋር በሰብዓዊ መብት ረገጣ በቁጥጥር ስር መዋላቸው ታውቋል።
በብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት ውስጥ በዳይሬክተርነት እስከ ሳምንቱ መጨረሻ ሲያገለግሉ የቆዩት አቶ መአሾ ኪዳኔ ቅዳሜ ከቀትር በኋላ በቁጥጥር ስር መዋላቸው ታውቋል።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በቅርቡ ከመደባቸው 58 ሰዎች ዝርዝር ውስጥ እኚህ የደህንነት መስሪያ ቤት ባልደረባ በቱርክ ኢስታንቡል ተሹመው እንደነበርም ተመልክቷል።
ሹመቱን ተከትሎ ከደህንነት መስሪያ ቤትና ከተለያዩ ስፍራዎች ጥያቄዎች ሲነሱ መቆየታቸውን የሚገልጹት የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ምንጮች መንግስት በጉዳዩ ላይ ማጣራት ካደረገ በኋላ ግለሰቡ በቁጥጥር ስር መዋላቸውን ገልጸዋል።
ከአቶ መአሾ ኪዳኔ ጋር ሌላው የብሔራዊ መረጃና ደህንነት ባልደረባ አቶ ሃዱሽ ካሳ በተመሳሳይ ባለፈው ቅዳሜ መታሰራቸው ይታወቃል።