የአዴት ከተማ ነዋሪዎች ባህር ዳር ገቡ

(ኢሳት ዲሲ–ታህሳስ 2/2011) በምዕራብ ጎጃም ዞን የይልማና ዴንሳ ወረዳ አዴት ከተማ ነዋሪዎች ያልተለወጠው አመራር በአስቸኳይ ስልጣን እንዲለቅ በመጠየቅ ለአቤቱታ ባህር ዳር ገቡ።

በወረዳው ባልተለወጡ የአስተዳደር አካላት እየተፈፀመ ያለውን ሙስናና የሰብዓዊ መብት ጥሰት እንዲቆም እንዲሁም  አመራሮቹ ለህግ እንዲቀርቡ  የአዴት ነዋሪዎች ጠይቀዋል።

ከአዴት ከተማ 42 ኪ.ሜ ርቀት ተጉዘው በ3 አውቶብሶች ባህርዳር የገቡት የአካባቢው ነዋሪዎች የክልሉ መንግስት አፋጣኝ ምላሽ እንዲሰጣቸው ጠይቀዋል።

በተደራጀ ሁኔታ አመራሩ ዝርፊያ ሲፈጽም ነበር፥  የተበላሸና ቤተዘመዳዊ የጥቅም አሰራር በህዝቡ ላይ ከፍተኛ ጉዳት አድርሷል ይላሉ ነዋሪዎቹ።

          በህወሀት ዘመን የነበረው የወረዳው አመራር ባለመለወጡ ህዝቡ ላይ የሚፈጸመው ጥቃት ቀጥሏል ሲሉም አቤቱታቸውን አቅርበዋል።

ባህርዳር የገቡት የአዴት ከተማ ነዋሪዎች ባለፉት ሰባት ወራት በተወካዮቻቸው አማካኝነት በተደጋጋሚ አቤቱታ ያቀረቡ ቢሆንም እስከአሁን ምላሽ አለማግኘታቸውን ገልጸዋል።

አመራሮቹ በኢትዮጵያ የሚታየው የለውጥ ጅምር ለአዴት ነዋሪዎች እንዳይደርስ እንቅፋት ሆነዋል ተብሏል።

በሙስና የተተበተቡ አመራሮች ከስልጣን ወርደው በህግ እንዲጠየቁ ካልተደረገ ህዝቡ ለከፍተኛ ተቃውሞ እየተዘጋጀ መሆኑንም  አቤቱታ አቅራቢዎቹ ገልጸዋል።

አፋጣኝ መልስ ካልተሰጣቸውም የበለጠ ቀውስ ሊከሰት ይችላል ባይ ናቸው።

ከዚህ ቀደምም በተመሳሳይ ሁኔታ በወረዳ አመራሮች ተበድለናል ያሉ የደቡብ አቸፈር ዱርቤቴ ከተማ ነዋሪዎች ሰሞኑን ባካሄዱት የተቃውሞ ሰልፍ 42 አመራሮችን ከስልጣን እንዲነሱ ማድረጋቸው ይታወሳል።

ያልተለወጡት አመራሮች ህዝቡ ላይ እንደሚዝቱ የገለጹት የአዴት ነዋሪዎች ” የዶ/ር አብይ የለውጥ ሃይል ለ3 ወር እንኳን በስልጣን ላይ ለማይቀጥለው ታጨበጭባላችሁ ‘’ በማለት እንደሚሳለቁም ተናግረዋል።

ከአዴት ባህርዳር የገቡት ነዋሪዎች በክልሉ ርዕሰ መስተዳደር ቢሮ፣ በአዴፓ ጽሕፈት ቤትና በአማራ ብዙሃን መገናኛ ድርጅት በመሄድ አቤቱታቸውን ማቅረባቸውን የደረሰን መረጃ ያመለክታል።