(ኢሳት ዲሲ–ሕዳር 26/2011) በኢትዮጵያ ባለፉት 11 ወራት ውስጥ የተከሰተው መፈናቀል ከየትኛውም የአለም ሀገር የበለጠ መሆኑን የተባበሩት መንግስታት ድርጅት አስታወቀ።
በግጭት እንዲሁም በድርቅና ጎርፍ ሳቢያ በምዕራባውያኑ 2018 የተፈናቀሉ ኢትዮጵያውያን ቁጥር ከ1 ነጥብ 4 ሚሊየን በላይ መሆኑም ተመልክቷል።
የተባበሩት መንግስታት የሰብአዊ ጉዳዮች ማስተባበሪያ ጽሕፈት ቤት /ኦቻ/ይፋ ባደረገው ሪፖርት መሰረት በአጠቃላይ የተፈናቃይ ኢትዮጵያውያን ቁጥር 2 ነጥብ 8 ሚሊየን ሲሆን ከዚህ ውስጥ ግማሽ ያህሉ የተፈናቀሉት ባለፉት 11 ወራት ብቻ ነው።
በተባበሩት መንግስታት ሪፖርት መሰረት የመፈናቀሉ ዋነኛ መንስኤ ግጭቶች ሲሆኑ ጎርፍና ድርቅን የመሰሳሉ ተፈጥሮአዊ ችግሮችም ለቀውሱ መባባስ አስተዋጽኦ ማድረጋቸውን አመልክቷል።
ከ2.8 ሚሊዮን ተፈናቃይ ኢትዮጵያውያን 2.2 ሚሊዮን የሚሆኑት በግጭት ሳቢያ የተፈናቀሉ ሲሆን ከግማሽ ሚሊየን የሚልቁት ድርቅና ጎርፍን በመሳሰሉ ተፈጥሮአዊ ችግሮች የተፈናቀሉ መሆናቸውንም ከሪፖርቱ መረዳት ተችሏል።
በአጠቃላይ 7.9 ሚሊዮን የሚሆኑት ኢትዮጵያውያን አስቸኳይ የምግብ ዕርዳታ የሚያስፈልጋቸው እንደሆነም ከሪፖርቱ መረዳት ተችሏል።
የውጭ ስደተኞችንም በማስተናገድ ኢትዮጵያ ከቀዳሚዎቹ የአፍሪካ ሃገራት አንዷ ነች ያለው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት በአሁኑ ወቅት 900 ሺህ ያህል ስደተኞች በኢትዮጵያ ይገኛሉ ብሏል።
ይህም ኢትዮጵያን ከዩጋንዳ ቀጥሎ በአፍሪካ ከፍተኛ የስደተኛ አስተናጋጅ አድርጓታል።