የቀድሞ የአሶሳ ከተማ ከንቲባን ጨምሮ 5 ባለስልጣናት በቁጥጥር ስር ዋሉ

(ኢሳት ዲሲ–ሕዳር 26/2011)በኦሮሚያና በቤንሻንጉል ጉምዝ አካባቢ ከተፈጠረው ግጭት ጋር በተያያዘ የቀድሞ የአሶሳ ከተማ ከንቲባን ጨምሮ 5 ባለስልጣናት በቁጥጥር ስር መዋላቸው ተገለጸ።

የፌደራል ፖሊስ ግብረሃይል በአካባቢው ባካሄደው ዘመቻ በቁጥጥር ስር የዋሉት ባለልጣናት ሰኔ 17/2010 በአሶሳ በተከሰተው ግጭት እንዲሁም በኦሮሚያና በቤንሻንጉል ወሰን ላይ በነበረው ግጭት የችግሩ ጠንሳሾች በመሆናቸው ነው ተብሏል።

በመንግስታዊዎቹ መገናኛ ብዙሃን እንደተዘገበው በቁጥጥር ስር ከዋሉት 5 ባለስልጣናት ውስጥ ከቀድሞው የአሶሳ ከንቲባ በተጨማሪ የክልሉ የጸጥታና አስተዳደር ዘርፍ ምክትል ሃላፊም ይገኙበታል።

ፌደራል ፖሊስ ዘመቻውን በመቀጠል ሌሎች ተጠርጣሪዎችንም ለመያዝ በመንቀሳቀስ ላይ መሆኑ ተመልክቷል።

እስካሁን በአጠቃላይ ከ200 በላይ ሰዎች በቁጥጥር ስር መዋላቸውም ተመልክቷል።

ጠቅላይ አቃቤ ህግ የምርመራ ቡድን ወደ ስፍራው መላኩን በሳምንቱ መጨረሻ ማስታወቁ ይታወሳል።

ጠቅላይ አቃቤ ህግ ህዳር 25/2011 ባወጣውና “መንግስት የህግ የበላይነትን ለማረጋገጥ የያዘውን ቁርጠኛ አቋም ከግብ እናደርሳለን” በሚል ርዕስ ባወጣው መግለጫ በተለያዩ የሃገሪቱ አካባቢዎች አቅደው ግጭት የቀሰቀሱና ህዝብን ለሞትና ለመፈናቀል የዳረጉትን ለህግ ለማቅረብ የምርመራ ቡድን መላኩን ይፋ አድርጓል።

ከሃገሪቱ ብሔራዊ የጸጥታ ምክር ቤት በሳምንቱ መጨረሻ በተሰጠ መግለጫ በተለይ በኦሮሚያና በቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል አዋሳኝ አካባቢ የተከሰተው ግጭት ከክልሎቹ አቅም በላይ ሆኖ በመገኘቱ የፌደራል የጸጥታ አካላት እንዲገቡ መደረጉን አስታውቋል።