የተከሰቱ ግጭቶችን የሚመረምር ቡድን ተሰማራ

(ኢሳት ዲሲ–ሕዳር 25/2011) በኢትዮጵያ በተለያዩ አከባቢዎች የተከሰቱ ግጭቶችን የሚመረምር ቡድን ማሰማራቱን ጠቅላይ አቃቤህግ አስታወቀ።

በእነዚህ ግጭት በተከሰተባቸው አካባቢዎች እጃቸውን ያስገቡ አካላትን የመለየት ስራ የሚያከናውን የመርማሪ ቡድን እንደሆነም ተመልክቷል።

በተደራጀ የኢኮኖሚ አሻጥር፣ሌብነትና፣ የሰብአዊ መብት ጥሰት የተሳተፉ ሕገ-ወጦችን ወደ ሕግ የማቅረቡ ሥራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የጠቀሰው የፌደራል ጠቅላይ ዓቃቤ ህግ የምርመራ ውጤቱን ለህብ በይፋ እንደሚያሳውቅም ገልጿል።

በየቦታው ግጭት አለ። በማንነትና በወሰን ይገባኛል መነሻ የሆኑት ግጭቶች እየተበራከቱ መምጣታቸው የሀገሪቱን ሰላምና ደህንነት አደጋ ላይ እንዳይጥለው መንግስት እርምጃ እየወሰድኩ ነው እያለ ነው።

የወሰንና ማንነት ጉዳይን የሚመለከት ኮሚሽን በማቋቋም ላይ መሆኑን ያስታወቀው መንግስት በየቦታው የሚነሱ ግጭቶችን ለማስቀረት በትኩረት እየሰራበት መሆኑን አስታውቋል። ከፌደራሉ አቃቤ ህግ የተገኘ መረጃ እንዳመለከተው እነዚህን ግጭቶች በተመለከተ የሚመረምር አንድ ቡድን ተዋቅሮ ተሰማርቷል።

የመርማሪ ቡድኑ ግጭት በተከሰተባቸው አካባቢዎች እጃቸውን ያስገቡ አካላትን የሚለይ ተግባር እንደሚያከናውን ነው የደረሰን መረጃ የሚያመለክተው።

ከአቃቤ ህግ መስሪያ ቤት የወጣው መረጃ ለይ እንደተመለከተው በተደራጀ የኢኮኖሚ አሻጥር፣ሌብነትና፣ የሰብአዊ መብት ጥሰት የተሳተፉ ሕገ-ወጦችን ወደ ሕግ የማቅረቡ ሥራ ተጠናክሮ እንዲቀጥል የመንግስት ውሳኔ አለ።

በሃገሪቱ በተለያዩ አከባቢዎች ለግል የገንዘብና የስልጣን ጥቅም  በሚል ግጭቶችን የሚቀሰቅሱ አካላት በግለሰብና በቡድን ተደራጅተው የሚገኙበትን ሁኔታ ለመርመር የተዋቀረው ቡድን ወደየአከባቢዎቹ ተሰማርቷል።

በተለይም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ አቅደው ግጭቶችን እየቀሰቀሱ ፣ለዜጎች ሞት፣ መፈናቀል፣ ከፍተኛ የንብረት ጉዳት እና የሰብአዊ መብት ጥሰት እያደረሱ የሚገኙ አካላትን ወደ ሕግ ለማቅረብ ችግሩ በተከሰተባቸው ሰፍራዎች የተደራጀ የምርመራ ቡድን በመላክ የምርመራዉ ሥራ በተጠናከረ መልኩ እየተከናወነ ይገኛል ብሏል ፌደራል ጠቅላይ አቃቤ ህግ።

የህግ የበላይነትን ማስከበር ለውጡን በሚፈለገው ዓይነትና ፍጥነት ለማኬድ ወሳኝ መሆኑ ሊሰመርበት ይገባል ያለው ፌደራል ጠቅላይ አቃቤህግ ከሕግ ውጭ የሆኑ አካላትን የሚፈጽሙትን ተግባር መንግስት የማይታገስና ለድርድር የማይቀርብ መሆኑንን የጠቅላይ አቃቤህግ መግለጫ አመልክቷል፡፡

የምርመራ ቡድኑ ስራውን አጠናቆ ከጨረሰ በኋላ ውጤቱ ለህዝብ ይፋ እንደሚሆንም ነው የፌደራል አቃቤ ህግ ያስታወቀው።

ሆኖም የምርመራ ቡዱኑ ውጤቱን የሚያቀርብበትን ጊዜ አልተገለጸም። አስተያየት ሰጪዎች የግጭት ቀጠና በሆኑ አከባቢዎች የምረመራ ቡድኑ ስራውን ለማከናወን የደህንነት ስጋት ይገድበዋል ይላሉ።

አካባቢዎቹ ባልተረጋጉበት ወቅት የሚደረግ ምርመራ የግጭቶቹን መንስዔና ተዋናያኖችን ለመለየት የሚቸግር በመሆኑ የፌደራል አቃቤ ህግ እንቅስቃሴ የፈጠነ ነው ሲሉ ይተቹታል። በጉዳዩ ላይ አስተያየታቸውን ለማግኘት በተደጋጋሚ ስልክ የደወልልናቸው የፌደራል ጠቅላይ አቃቤ ህግ አቶ ብርሃኑ ጸጋዬ ምላሽ ሊሰጡን አልቻሉም።