በጭልጋ በተቀሰቀሰ ግጭት በሰውና ንብረት ላይ ጉዳት ደረሰ

(ኢሳት ዲሲ–ሕዳር 25/2011) በማዕከላዊ ጎንደር ዞን ጭልጋ በተቀሰቀሰ ግጭት በሰውና ንብረት ላይ ጉዳት መድረሱ ተገለጸ።

ከቅማንት ጥያቄ ጋር በተያያዘ በተነሳው በዚሁ ግጭት የአንድ ሰው ህይወት ሲያልፍ 8 ሰዎች መቁሰላቸውን የዞኑ አስተዳዳሪ ገልጸዋል።

ፋይል

በርካታ ቤቶች መቃጠላቸውን እንዲሁም ዝርፊያ መፈጸሙንም አስተዳዳሪው አስታውቀዋል።

ጥቃቱን በቅማንት ስም በስውር የሚንቀሳቀሱ ቡድኖች የፈጸሙት እንደሆነ ተመልክቷል።

በተያያዘ ዜና በማዕከላዊ የጎንደር ዞን ጠገዴ ወረዳ በአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ላይ በተፈጸመ የቦንብ ጥቃት ሁለት ተማሪዎች መገደላቸውን የደረሰን መረጃ አመልክቷል።

ጥቃቱ የደረሰው ትላንት ነው። የአማራ ብዙሃን መገናኛ ድርጅት የማዕከላዊ ጎንደር ዞን ዋና አስተዳዳሪ የሆኑትን አቶ ብርሃኑ ጣምያለውን ጠቅሶ እንደዘገበው።

በቅማንት ስም በህቡዕ ተደራጅተው የሚንቀሳቀሱ ቡድኖች ጥቃት ፈጽመዋል።

በቅርቡ የአማራ ክልል የጸጥታ ቢሮ ሃላፊ ብርጋዴር ጄነራል አሳምነው ጽጌን ጨምሮ በ10 የአማራ ክልል ባለስልጣናት ላይ ክስ አቀረብኩ ያለውና ራሱን የቅማንት ጥያቄ አስመላሽ ኮሚቴ ብሎ የሚጠራው አካል ካለፈው መስከረም ወር ወዲህ በርካታ የቅማንት ተወላጆች መገደላቸውን፣ ቤት ንብረታቸው መቃጠሉንና መዘረፉን መጥቀሱ የሚታወስ ነው።

ትላንት ጭልጋ ላይ የተፈጸመው ጥቃት የአንድ ሰው ህይወት አጥፍቷል። 8 ሰዎችም ቆስለው ወደ ህክምና ማዕከላት ተወስደዋል።

በጥቃቱ 39 ቤቶች መቃጠላቸውን 50 ቤቶችና 9 ወፍጮ ቤቶች ደግሞ መዘረፋቸውን የዞኑ ዋና አስተዳዳሪ ለአማራ ብዙሃን መገናኛ ድርጅት በሰጡት መግለጫ ላይ አስታውቀዋል።

አስተዳዳሪው እንዳሉት በዛሬው ዕለት አከባቢውን በመቆጣጠር ጥቃቱ እንዲቆም ተድርጓል።

በዚህ ተግባር የተሰማሩ 153 ሰዎችም በተጠርጣሪነት መለየታቸውንንና ለህግ ለማቅረብ በዝግጅት ላይ መሆናቸውን አስተዳዳሪው አቶ ብርሃኑ ገልጸዋል።

የክልሉ ፖሊስ ከፌደራል ፖሊስ ጋር በመሆን የሰላም ማስጠበቅ ስራውን እያከናወነ ነው ብለዋል አስተዳዳሪው።

ይህ በእንዲህ እንዳለም በጠገዴ ወረዳ በአንደኛ ድረጃ ትምህርት ቤት የተቀበረ ፈንጂ በተማሪዎች ላይ የሞትና የመቁሰል አደጋ ማድረሱን ለማወቅ ተችሏል።

በወረዳው ቡርሄ ቀበሌ በሚገኘው የአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ቅጥር ግቢ ውስጥ በደረሰው በዚሁ የፈንጂ አደጋ ሁለት ተማሪዎች ወዲያውኑ ህይወታቸው ማለፉን የደረሰን መረጃ አመልክቷል።

6 ተማሪዎችም ከባድ ጉዳት ደርሶባቸዋል። እነዚህ ጉዳት የደረሰባቸው በሳንጃ ከተማ በሚገኝ የህክምና ማዕከል ቢገቡም ጉዳቱ ከባድ በመሆኑ ወደ ጎንደር ሆስፒታል መላካቸውም ታውቋል።

ፖሊስ ምርመራ እያደረገ መሆኑን ከመግለጽ ያለፈ ስለፈንጂ ጥቃቱ የሰጠው ዝርዝር መረጃ የለም።