(ኢሳት ዲሲ–ሕዳር 20/2011)በኦሮሚያና ቤንሻንጉል ጉምዝ አዋሳኝ መንደሮች በተነሳ ግጭት በርካታ የፖሊስ አባላትና እንዲሁም ነዋሪዎች መገደላቸው ተገለጸ።
የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት ኮሚኒኬሽን ቢሮ እንዳስታወቀው በምስራቅ ወለጋ ሊሙ ወረዳ በተከሰተው ግጭት ከፍተኛ የንብረት ውድመትም ተከስቷል።
ስልጣን ያለአግባብ ሲጠቀሙ ፣ የኢኮኖሚ ዝርፊያ ሲያካሂዱ የነበሩና ይህ ጥቅማቸው ከእጃቸው የወጣ አካላት ትግሉን ወደ ኋላ ለመመለስ በሁሉም ስፍራዎች ግጭቶች እንዲከሰቱ እያደረጉ ነው ሲል የኦሮሞ ዲሞክራሲያዊ ፓርቲ ኦዴፓ አስታውቋል።
ኦዴፓ ዛሬ ባደረገው አስቸኳይ ስብሰባ እነዚህ ሃይሎች በሰው ልጅ ላይ መፈፀም የሌለባቸው አሰቃቂ ወንጀሎች እንዲፈፀሙና ዜጎች ከቤት ንብረታቸው እንዲፈናቀሉ በማድረግ የክልሉን ሰላም ለማደፍረስ እየሰሩ ነው ብሏል።
በሁለቱ ክልሎች አዋሳኝ አካባቢዎች የተነሳው ግጭት ከ100 በላይ ሰዎችን ህይወት አጥፍቶ፣ በመቶሺዎች አፈናቅሎም መረጋጋት አልቻለም።
ዛሬ እንደተሰማውም ቁጥራቸው በርካታ የሆኑ የኦሮሚያ ፖሊስ አባላት ተገድለዋል።
ሰላማዊ ሰዎችም ሕይወታቸው አልፏል። የኦሮሚያ ክልል የመንግስት ኮሚኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ እንዳስታወቀው ምስራቅ ወለጋ ዞን እና በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል አዋሳኝ አካባቢ በተፈጠረ ግጭት የሰው ህይወትና ንብረት ላይ ጉዳት ደርሷል።
ቢሮው የደረሰውን ጉዳት በቁጥር ሳይገልጽ ዝርዝር መረጃ በቅርቡ ይፋ ይደረጋል ብሏል።
የተለያዩ የመረጃ ምንጮች እንደሚያመላክቱት ደግሞ የተገደሉት ፖሊሶች ቁጥር በትንሹ 10 ይሆናል።
ከ15 በላይ ሰላማዊ ሰዎችም ሳይገደሉ እንደማይቀር ነው ከምንጮች መረጃ ለማወቅ የተቻለው።
የኦሮሚያ ክልል ኮሚኒኬሽን ቢሮ ምክትል ሃላፊ አቶ ዴሬሳ ተረፈ ለፋና ብሮድካስት እንደገለጹት ከትላንት በስቲያ ማክሰኞ በምስራቅ ወለጋ ዞን ሊሙ ወረዳ ልዩ ስሙ አርቁምቢ በተባለ አከባቢ በነዋሪዎች እና በኦሮሚያ ፖሊስ አባላት ላይ አሰቃቂ ወንጀል ተፈጽሟል።
የተገደሉት ፖሊሶች አስከሬኖች ነቀምት ሲገቡ ነዋሪው አደባባይ ሰልፍ በመውጣት ቁጣውን የገለጸ ሲሆን ግጭትም ተፈጥሮ የአንድ ሰው ህይወት ማለፉ ታውቋል።
የፖሊሶችንና የሰላማዊ ነዋሪዎችን አሰቃቂ ግድያ ተከትሎም በኦሮሚያ ክልል በተለይም በምዕራብ አንዳንድ ከተሞች ነዋሪዎች የተቃውሞ ሰልፍ በማካሄድ ቁጣቸውን ሲገልጹ ውለዋል።
መንግስት በአስቸኳይ ግድያውንና መፈናቀሉን እንዲያስቆም ጠይቀዋል። በተመሳሳይ በሶማሌና ኦሮሚያ ጭናክሰን ላይ በተፈጸመ ጥቃት 11 ሰዎች መገደላቸው ታውቋል።
በአንዳንድ በኦሮሚያ ክልልና አዋሳኝ አከባቢዎች እየተፈጸሙ ያሉት ግድያዎች እየተበራከተ መምጣቱን ተከትሎ የኦሮሞ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ ኦዴፓ አስቸኳይ ስብሰባ ተቀምጦ ውሳኔ አስተላልፏል።
ጠንከር ከረር ያለ ማስጠንቀቂያም ሰትቷል። ያለአግባብ ሲጠቀሙ ፣ የኢኮኖሚ ዝርፊያ ሲያካሂዱ የነበሩና ይህ ጥቅማቸው ከእጃቸው የወጣ አካላት ትግሉን ወደ ኋላ ለመመለስ በሁሉም ስፍራዎች ግጭቶች እንዲከሰቱ አድርገዋል ያለው ኦዴፓ እነዚህ አካላት እነማን እንደሆኑ ፍንጭ ከመስጠት ተቆጥቧል።
በሰው ልጅ ላይ መፈፀም የሌለባቸው አሰቃቂ ወንጀሎች እንዲፈፀሙና ዜጎች ከቤት ንብረታቸው እንዲፈናቀሉ በማድረግ የክልሉን ሰላም ለማደፍረስ እየሰሩ ነው ብሏል የኦሮሞ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ ኦዴፓ።
እነዚህ የተደራጁ ሌቦች በሚሸርቡት ሴራ የኦሮሞን ህዝብ ከሌሎች ብሄር ብሄረሰቦች ጋር ለማጋጨት ሲሞክሩ እቅዳቸው ሲከሽፍ ደግሞ በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ውስጥ ያሉ ተማሪዎችን ለማጋጨት እየሰሩ እንደሚገኙም ፓርቲው ገልጿል።
ከሰሞኑ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ውስጥ በሰላም የሚኖሩ ኦሮሞዎችን፣ እንዲሁም የሶማሌ ክልል ወሰን አካባቢ በሞያሌ፣ በጭናክሰን እና ባቢሌ ወረዳ በሚኖሩ ሰላማዊ ህዝቦች ላይ አሰቃቂ የሆነ ግድያ እንዲሁም ከቤት ንብረት የማፈናቀል ወንጀል እየፈፀሙ ነው ያለው ኦዴፓ ለተሰዉ ሰላማዊ ዜጎችና የፀጥታ አካላት ያለኝን አክብሮት እገልጻለሁ፡ ለተሰዉ ዜጎች ቤተሰቦች እና ወዳጆች መፅናናትን እመኛለሁ ብሏል በመግለጫው።
ኦዴፓ እነዚህ አካላት በዝምታ እንደማይመለከት በመግለጽ ጠንካራ ማስጠንቀቂያም አስተላልፏል።
ይህ የመቃብር አፋፍ ላይ የደረሰው ህልማቸው ወደ መቃብር ይወርዳል እንጂ መቼም ቢሆን የኦሮሚያ ክልልን የብጥብጥ እና የጦርነት አውድማ አያደርጓትም ያለው ኦዴፓ የክልሉን ሰላም በቅርብ ቀናት ውስጥ በማረጋገጥ ህዝቡን ከሰቀቀን እንደምንገላግል ምንም ጥርጥር የለንም ሲል መግለጫውን አጠናቋል።