በአፋር ክልል በተቀሰቀሰ ግጭት አንድ የአፋር ወጣት ተገደለ

(ኢሳት ዲሲ–ሕዳር 24/2011) በአፋር ክልል በመሬት ይገባኛል ጥያቄ ኤል ውሃ አካባቢ ቡርካ በሚባል ቦታ በተቀሰቀሰ ግጭት ሰላም ለማስከበር በሚል ጣልቃ በገባ የመከላከያ ሰራዊት አንድ የአፋር ወጣት መገደሉን ለኢሳት የደረሰ መረጃ አመልክቷል።

በአፋር ዛሬ የሚጀመረውንና አብዛኛውን አመራሮችን ያሰናብታል ተብሎ የሚጠበቀው የክልሉ ገዢ ፓርቲ ጉባዔውን በሚያካሂድበት ወቅት ዋዜማ የተቀሰቀሰው ግጭት ሶስተኛ ቀኑን መያዙ ታውቋል።

ፋይል

ጉባዔውን በሁከት በማጀብ የአቶ ስዩም አወል ቡድን የሚፈጽመው ሴራ ሳይሆን አይቀርም ተብሏል።

በአፋር ዛሬ በሚጀመረው ጉባዔ አዳዲስ አመራሮች ወደ ስልጣን እንዲመጡ ግፊት የሚያደርግ ሰላማዊ ሰልፍ በተለያዩ የአፋር ከተሞች መካሄዱን ለማወቅ ተችሏል።

በአፋር ክልል ነው። በኤል ውሃና ባቲ ከተሞች መካከል በሚገኝ ስፍራ ነው።

በዚህ ስፍራ ለዘመናት የቆየ ግጭት በተለይም በኦሮሞና አፋር ነዋሪዎች መካከል ይደረግ እንደነበር ነው የሚነገረው።

በዚህም በርካታ ሰዎች ከሁለቱም ወገኖች የተገደሉበት ክስተት ተፈጥሮ አልፏል።

በሁለቱም ወገኖች ያሉ የወረዳ አመራሮች በሚጭሩት እሳት ህዝቡ እየተማገደ ህይወት በሚያጠፋ ግጭት ውስጥ ይገባ እንደነበር የሚገልጹት ምንጮች ዘንድሮም በተፈጠረው ፖለቲካዊ ውጥረት ለውጥን የማይፈልጉ አመራሮች ግጭቱ እንዲቀሰቀስ አድርገውታል ነው የተባለው።

ልዩ ስፍራው ቡርካ የተሰኘውን አካባቢ በይገባኛል ሰበብ ከሁለት ቀናት በፊት በተነሳው ግጭት በመከላከያ ሰራዊት አንድ የአፋር ወጣት መገደሉን የደረሰን መረጃ አመልክቷል። ከኤልውሃ ባቲ የሚወስደው መንገድም መዘጋቱ ተገልጿል።

ጉዳዩ ዛሬ ከሚጀመረው የአፋር ገዢ ፓርቲ ጉባዔ ጋር ሊገናኝ እንደሚችል የሚገልጹት ምንጮች በህዝቡ ዘንድ ከፍተኛ ተቃውሞ የገጠመው የአቶ ስዩም አወል አስተዳደር ቀውስ በመፍጠር በስልጣን ለመቆየት የጎነጎኑት ሴራ ሊሆን ይችላል ሲሉ አንዳንድ የአፋር የሰብዓዊ መብት ተቆርቋሪዎች ይናገራሉ።

በህዝብ ተቃውሞ በመጨረሻም ከስልጣን እንዲወርዱ ፓርቲያቸው ውሳኔ ያስተላለፈባቸው አቶ ስዩም አወል በየወረዳው የሰገሰጓቸውን የእሳቸውን ሰዎች በማደራጀት የጉባኤውን ውጤት ለመቀየር እየተንቀሳቀሱ ነው ሲሉ የአፋር ተሟጋቾች ይከሷቸዋል።

እሳቸውን ጨምሮ አብዛኛውን የስራ አስፈጻሚና የማዕከላዊ ኮሚቴ አባላትን ያስወገደው የአፋር ገዢ ፓርቲ አዳዲስና ወጣት አመራሮችን ወደፊት እንዲያመጣቸው ጫና እየተደረገ ነው።

ከጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ጀምሮ ለውጥ አፋር ላይ እንዲጀመር የሚደረገው ጫና በበረከተበት በዚህ ሰሞን የአቶ ስዩም አወል ቡድንም በመጨረሻው ሰዓት እጁን ላለመስጠት እየተንገታገተ መሆኑ ይነገራል።

በህወሃት የሚደገፈው የአቶ ስዩም አወል ቡድን የጎሳ ግጭት ለመጫርም አንዳንድ ርምጃዎችን በመውሰድ ላይ በመሆኑ የአፋር ህዝብ በንቃት እንዲጠብቅ ጥሪ ቀርቧል።

ዛሬ የተጀመረው ጉባዔ እንዳይጠለፍና በሀገር ደረጃ የተጀመረውን ለውጥ በአፋር ምድር ላይ እንዲካሄድ የሚያደርግ እንዲሆን በህዝቡ ከፍተኛ ግፊት በመደረግ ላይ ነው።

በተለያዩ የአፋር ከተሞች ህዝቡ ሰላማዊ ሰልፍ በማድረግ የአቶ ስዩም አወል እጆች ከጥፋት እንዲቆጠቡ መልዕክት ተላልፏል።

አዳዲስ አመራሮች እንዳይመጡ በአቶ ስዩም በኩል እየተደረገ ያለው እንቅስቃሴ የተወገዙበት የተቃውሞ ሰልፎች ተጠናክረው ቀጥለዋል።