(ኢሳት ዲሲ–ሕዳር 19/2011)በአቶ ሌንጮ ለታ የሚመራው ኦዴግ በጠቅላይ አብይ አህመድ ከሚመራው ኦዴፓ ጋር ለመዋሀድ የመግባቢያ ሰነድ ተፈራረሙ።
የኦሮሚያ ክልል መንግስት ፕሬዝዳንትና የኦዴፓ ምክትል ሊቀመንበር አቶ ለማ መገርሳ ከአቶ ሌንጮ ለታ ጋር ስምምነቱን ፈርመዋል።
ለኦሮሞ ህዝብም ሆነ ለመላው የኢትዮጵያ ህዝብ ከመከፋፈል ይልቅ ተሰባስቦ መስራቱ የበልጥ ትርጉም ይኖርዋል በማለት መግለጫ የሰጡት አቶ ለማ መገርሳ እለቱን ታሪካዊ ሲሉ ገልጸውታል።
በሃይማኖት በሰፈርና በጎሳ የተከፋፈሉ ፓርቲዎች እንዲሰባሰቡም ጥሪ አቅርበዋል።
አቶ ሌንጮ ለታ በበኩላቸው በሁኔታው መደሰታቸውን ገልጸው በኢትዮጵያ ከዚህ ቀደም የጨነገፉ እድሎች እንዳይደገሙ ከቀደመው ስህተት መማር እንደሚገባ አሳስበዋል።
የኦሮሞ ነጻነት ግንባር/ኦነግ/ የመጀመሪያው ሊቀመንበር የነበሩትን ዶክተር ዲማ ነገዎን በምትክል ሊቀመንበርነት የያዘውና የኦሮሞ ዲሞክራሲያዊ ግንባር/ኦዴግ/በ1983 በኢትዮጵያ በተካሄደው የሽግግር ስርአት ውስጥ ከዋና ተዋናዮቹ አንዱ የነበሩትና የሽግግሩን ወቅት ቻርተር ከአቶ መለስ ዜናዊና ከአቶ ኢሳያስ አፈወርቄ ጋር ኤርትራ ሰንአፌ ውስጥ ያረቀቁት አቶ ሌንጮ ለታ በሊቀመንበርነት ይመሩታል።
የኦሮሞ ዲሞክራሲያዊ ግንባር/ኦዴግ/መሪዎች ከኦሮሞ ነጻነት ግንባር/ኦነግ/ ከተለዩ አመታት አስቆጥረዋል።
ሆኖም የኦሮሞ ነጻነት ግንባር/ኦነግ/ከ8 አመታት በፊት ለሁለት ሲከፈል ሁለቱን ወገኖች በሽምግልና ወደ አንድ ለማምጣት በአደራዳሪነት ተንቀሳቅሰዋል።
በአቶ ዳውድ ኢብሳ በሚመራው ኦነግና በብርጋዴር ጄኔራል ከማል ገልቹ በሚመራው ኦነግ መካከል ያለውን ችግር ለመፍታት የተጓዙበት ርቀት ኦነግ በአንድ ስም በሁለት ቡድን እንደማይቀጥል ያደረገው ቢሆንም ሁለቱን ወገኖች ማስማማት ግን አልተቻለም።
አቶ ዳውድና ጄኔራል ከማል ገልቹ በየፊናቸው ሲቀጥሉ ሸምጋዮቹ እነ አቶ ሌንጮ ለታ ደግሞ የኦሮሞን ሕዝብ መብት በኢትዮጵያ አንድነት ውስጥ ለማስከበርና መገንጠል መፍትሄ አያመጣም በሚል ከ5 አመት በፊት እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር በ2013 የኦሮሞ ዲሞክራሲያዊ ግንባርን መሰረቱ።
ከሌሎች የኢትዮጵያ ሃይሎች ጋር ተባበረው ለመስራት በመወሰንም በነሐሴ 2009 ከአርበኞች ግንቦት 7 ጋር የመግባቢያ ሰነድ ተፈራረሙ።
በህዳር 2009 ሁለቱ ድርጅቶች የአፋር ሕዝብ ፓርቲንና የሲዳማ ሕዝብ ዲሞክራሲያዊ ንቅናቄን በመጨመር የኢትዮጵያዊ ሃገራዊ ንቅናቄን መሰረቱ።
በኢትዮጵያ ውስጥ የመጣውን ለውጥ በቅድሚያ በመደገፍና በአዲሱ የለውጥ ሃይል ላይ እምነት በማሳደርም የኦዴግ መሪዎች በግንቦት ወር 2010 ወደ ኢትዮጵያ ተመልሰዋል።
የኦሮሞ ዲሞክራሲያዊ ግንባር/ኦዴግ/በተመሰረተ በሁለት አመት ጊዜ ውስጥ ከአንዳንድ የመንግስት ሃላፊዎች በተገባላቸው ቃል የመንግስት ባለስልጣናትን ለማነጋገር በመጋቢት ወር 2007 አመተ ምህረት ወደ ኢትዮጵያ ተጉዘው የነበሩት አቶ ሌንጮ ለታ የሚያናግራቸው አጥተው በአራት ቀናት ውስጥ ከሃገር እንዲወጡ ተደርገዋል።
የኦሮሞ ነጻነት ግንባር/ኦነግ/አመራር የነበሩትን አቶ ኢብሳ ጉተማን ለማስፈታት ከ20 አመት በፊት ወደ ኢትዮጵያ በተጓዙበትም ወቅት ራሳቸውም ጭምር መታሰራቸውን ማስታወስ ይቻላል።
በኋላም በይቅርታ በሳምንት ጊዜ ውስጥ ከሃገር እንዲወጡ ተደርገዋል።
በግንቦት 2010 ከሌሎች አመራሮች ጋር ወደ ኢትዮጵያ የተጓዙት አቶ ሌንጮ ለታ ዛሬ ወደ እስር ቤት አልተመለሱም።
እንደከዚህ ቀደሙ ከሃገራቸው አልተባረሩም፣ይልቁንም የራሳቸው ድርጅት ኦዴግ የገዢው ፓርቲ አካል ከሆነው ኦዴፓ ጋር ለመዋሃድ የመግባቢያ ሰነድ ፈረሙ።
የውህደት ስምምነቱን ከአቶ ሌንጮ ለታ ጋር የተፈራረሙት የኦዴፓ ምክትል ሊቀመንበርና የኦሮሚያ ክልል ፕሬዝዳንት አቶ ለማ መገርሳ እለቱን “ለኔ ታሪካዊ ነው”ሲሉ ጠቅሰውታል።
ለኦሮሞ ሕዝብም ሆነ በአጠቃላይ ለኢትዮጵያ ሕዝብ ትልቅ ትርጉም ያለው አቅምና ጉልበታችንን የሚጨምር ርምጃ ነው ሲሉ ውህደቱን ገልጸውታል።
እነ አቶ ሌንጮ ለታ ብዙ ውጣ ውረዶችን ያለፉ የኦሮሞ ትግል መሃንዲሶች ናቸው ያሉት አቶ ለማ መገርሳ እነዚህ ከኦዴፓ ጋር መዋሃዳቸው ድርጅታችንን ሙሉና ጠንካራ ያደርገዋል ብለዋል።
በኦሮሞ ውስጥ ከአስር በላይ ድርጅቶችም በኢትዮጵያ በአጠቃላይ ከ70 በላይ ፓርቲዎች በሃይማኖት፣በጎሳና በሰፈር ከሚከፋፈሉ ሰብሰብ ብለው እንዲቆሙም አቶ ለማ መገርሳ ጥሪ አቅርበዋል።
የኦዴግ ሊቀመንበር አቶ ሌንጮ ለታ በበኩላቸው በስነስርአቱ ላይ ባደረጉት ንግግር ኢትዮጵያ ወደ ዲሞክራሲ ለመሻገር ጥሩ ጊዜ ላይ መሆኗን ገልጸዋል።
የእስከዛሬዎቹ ተስፋዎች የመከኑት በፍጥነት ስለምንጣላና ከስህተታችንም ስለማንማር ነው ብለዋል።
አቶ ሌንጮ የተጀመረውን ዲሞክራሲያዊ ሒደት ለማስቀጠል ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ብቃትም ቁርጠኝነትም አላቸው ብለዋል።
ሌሎች ድርጅቶችም እንደዚሁ እንዲሰባሰቡ ጥሪ አቅርበዋል።
ወደ ሃገር ቤት ከተመለሱ የኦሮሞ ድርጅት መሪዎችና አባላት ጄኔራል ከማል ገልቹ፣ጄኔራል ሃይሉ ጎንፋና ኮለኔል አበበ ገረሱ በኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት ውስጥ በጸጥታው ዘርፍ በሃላፊነት ላይ ተመድበው በመስራት ላይ መሆናቸው ይታወቃል።