አብዴፓ 12 አመራሮችን ከሃላፊነት እንዲነሱ ወሰነ

(ኢሳት ዲሲ– ህዳር 19/2011)የአፋር ብሔራዊ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ /አብዴፓ/ ማዕከላዊ ኮሚቴ የክልሉን ፕሬዝዳንት ጨምሮ 12 አመራሮችን ከሃላፊነት እንዲነሱ ውሳኔ አስተላለፈ።

የክልሉ ፕሬዝዳንት  ውሳኔውን  አልቀበልም ማለታቸው ተሰምቷል።

ትላንት የፓርቲው ማዕከላዊ ኮሚቴ ስብሰባ አድርጎ እንዲሰናበቱ ውሳኔ የሰጠባቸው አመራሮች ባለፈው ሳምንት ከጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ጋር በአዲስ አበባ የተደረገውን ስምምነት ተከትሎ ነው።

ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ክልሉ በወጣት አመራሮች መተካት አለበት የሚል አቋም ላይ ደርሰው ለአብዴፓ አመራሮች መግለጻቸው የሚታወስ ነው።

በአፋር ከሁለት ወራት በላይ በዘለቀው ህዝባዊ ተቃውሞ በአቶ ስዩም አወል የሚመራው የአፋር ክልል አስተዳደር በአስቸኳይ ስልጣን እንዲለቅ ሲጠየቅ ቆይቷል።

ማዕከላዊ ኮሚቴው ስብሰባ አድርጎ ለህዝቡ ጥያቄ ምላሽ እንዲሰጥ በተደረገው ስምምነት መሰረት በትላንትናው ዕለት ፕሬዝዳንቱን አቶ ስዩም አወልን፣ የቀድሞ ፕሬዝዳንትና የማዕከላዊ ኮሊቴ አባል አቶ ኢስማዔል አሊ ሴሮና ሌሎች 10 አመራሮች ከሃላፊነታቸው እንዲነሱ መደረጉን የደረሰን መረጃ ያመለክታል።

ሆኖም አቶ ስዩም አወል የፓርቲው ማዕከላዊ ኮሚቴ ያሳለፈውን ወሳኔ አልቀበልም ማለታቸው ተመልክቷል።

የአፋር ውዝግብ አዲስ ምዕራፍ ይዟል። ያለማቋረጥ ለሁለት ወራት የዘለቀው የህዝቡ ተቃውሞ ሰሚ ጆሮ አግኝቶና ለውጥ በሚያመጣበት ዋዜማ የችግሩ ተዋናይ ናቸው ተብለው ጣት የሚጠነቆልባቸው የክልሉ ፕሬዝዳንት አቶ ስዩም አወል ይዘው የተነሱት አቋም ሌላ ቀውስ እንዳይፈጥር ስጋቱ ከየአቅጣጫው እየተሰማ ነው።

አቶ ስዩም አወል ባለፈው ሳምንት በአዲስ አበባ ከጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ጋር ከተወያዩና ክልሉ አዲስ አመራር እንደሚያስፈልገው ከስምምነት ከደረሱ በኋላ ወደ ሰመራ ሲመለሱ ሀሳባቸውን መቀየራቸውን ነው የኢሳት ምንጮች የሚገልጹት።

አቶ ስዩም ከአዲስ አበባ መልስ ከህወሀት መሪዎች ጋር ሲገናኙ እንደነበርና አቶ ቢተው በላይ የተባሉ የህወሀት አመራር በአካል ሰመራ ድረስ መጥተው ድጋፍ በመስጠት ለውጡን እንዳይቀበሉ እንደመከሯቸው ነውምንጮች የገለጹት።

በህወሃት የልብ ልብ የተሰማቸው አቶ ስዩም አወል ከስልጣን የሚለቁ እንኳን ቢሆን በምትካቸው የሚቀመጡት የእሳቸውን ዘመድ እንዲሆን ለማድረግ እንቅስቃሴ መጀመራቸው ታውቋል።

በዚህ መካከል በትላንትናው ዕለት የአፋር ብሔራዊ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ አብዴፓ የስራ አስፈጻሚ ኮሚቴና የማዕከላዊ ኮሚቴ በተናጠል ባደረጉት ስብሰባ አቶ ስዩም አወልና ሌሎች 11 አመራሮች የፊታችን ህዳር 23 ከሚካሄደው ጉባዔ በፊት ከሃላፊነት እንዲነሱ ውሳኔ አስተላልፈዋል። አቶ ስዩም አወል ግን አለተቀበሉም።

የአፋር ክልል ሁለተኛው ከትግራይ ቀጥሎ ለህወሀት ሁለተኛው ቤቱ ነው ይባላል።

የህወሃት ባለሃብቶች ጨውንና ፖታሺየምን ጨምሮ በክልሉ የሚገኙ ማዕድናትን በበላይነት ተቆጣጥረው እንዲይዙ የክልሉን ገዢ ፓርቲ ከመቀሌ በሚሰጥ መመሪያ የሚንቀሳቀስ እንዲሆን ተደርጎ ከ20 ዓመታት በላይ ቆይቷል።

ከቀዳሚው የክልሉ ፕሬዝዳንት አቶ ኢስማዔል አሊ ሴሮ ስልጣኑን የተረከቡት አቶ ስዩም አወል ከአፋር ይልቅ የህወሃትን ጥቅም በማስከበር የክልሉ ሀብትና በጀት ሲያዘርፉ ቆይተዋል የሚለው ክስ እየተጠናከረ መጥቷል።

ከሁለት ወራት በላይ የዘለቀው ህዝባዊ ተቃውሞ ዋና መነሻም የህወሃት እጅ ከአፋር ላይ እንዲነሳ የሚጠይቅ ነው።

ከጠቅላይ ሚኒስር አብይ አህመድ ጋር የተደረገውን ስምምነት ወደ ጎን አድርገው መቀሌ ከመሸጉት የህወሀት መሪዎች ጋር ግንኙነታቸውን የቀጠሉት አቶ ስዩም አወል በስልጣን የማይቆዩ ከሆነ አልያም እሳቸው ከጀርባ የሚዘውሩት ሌላ ሰው የማይሾም ከሆነ የጎሳ ግጭት ለመቀስቀስ መዘጋጀታቸውም ይነገራል።

ለዚህም የህወሀት ድጋፍ አልተለያቸውም። የአፋር አክቲቪስቶች ግን የህወሀት እጅ በአፋር ላይ ከእንግዲህ አቅም የለውም ይላሉ።

አቶ ስዩም አውል ከስልጣን አልወርድም ከወረድኩም ለዘመድ ሰጥቼ ነው በሚለው አቋማቸው ጸንተዋል።

ህዳር 23 ጉባዔው እየተጠበቀ ነው። አቶ ስዩም አወል በህወሀት ደጀንነት ጉባዔውን ከህዝቡ ፍላጎት ውጪ እንዳይቀለብሱት የፌደራል መንግስቱ ተገቢውን ትኩረት እንዲሰጠው መልዕክት እየተጠየቀ ነው።