(ኢሳት ዲሲ–ህዳር 6/2011)ወንጀለኞችን እያደኑ ለፍርድ የማቅረቡ ተግባር እንደሚቀጥል ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አሕመድ ገለጹ።
ኢትዮጵያ ቢሊየን ብር የመዘበሩ በነጻነት የሚኖሩባትና አንድ ብር አጥተው ከቆሻሻ ገንዳ ምግብ የሚፈልጉ ሁለት አይነት ዜጎች ሊኖሩባት አይገባም ሲሉም አሳስበዋል።
አራዊት እንኳን የማይፈጽመውን ኢሰብአዊ ድርጊት የሚፈጽሙ ሰዎች ለወገናቸው ሊራሩ አይችሉም ሲሉም ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አሕመድ እየተወሰደ ያለውን መንግስታዊ ርምጃ በተመለከተ “ካንሰርን በጋራ እንከላከል” በሚል ርዕስ በበተኑት ባለ አራት ገጽ ጥሪ የትላንት ወንጀለኞች መደበቂያቸው ጫካ ቢሆንም የዛሬዎቹ መሸሸጊያቸው ብሔር ወይንም ጎሳ ሆኗል ሲሉ ተችተዋል።
ሆኖም ወንጀለኞች ጥቅም እስካገኙ ድረስ ወገኔ ለማለት የማይራሩ ናቸው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ለወንጀለኞች ወገናቸው ኪሳቸውና የጥቅም ተጋሪያቸው ብቻ ነው ብለዋል።
“የጥንት ሽፍቶች መሸሸጊያቸው ጫካ ነበር ዛሬ ግን ጫካው አልቋልና መደበቂያቸውን ብሔር ወይንም ጎሳ ለማድረግ ይኳትናሉ።”ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በጽሁፋቸው።
“ሲበሉ ዞር ብለው ያላዩትን ሕዝብ ሲያዙ ይፈልጉታል፣ራሳቸው የዘረፉት ሕዝብ ሲደርስባቸው ለመደበቂያነት ይፈልጉታል” ሲሉም በጽሁፋቸው ላይ ትችታቸውን አቅርበዋል።
የወንጀለኛ መመሪያ ጥቅምን ለብቻ መከራን በጋራ የሚል ነው በማለት የቀጠለው የጠቅላይ ሚኒስትሩ ጽሁፍ ወንጀለኛ ወገንም፣ ብሔርም፣ ዘርም፣ሞራልም የለውም ሲሉም ገልጸዋል።
“አሁን የተጀመረው ስራ ሃገር የገደሉ ወንጀለኞችን እነርሱ ለሌላው በነፈጉት ፍትህ ፊት የማቅረብ ስራ ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አሕመድ እነርሱ በሔዱበት መንገድ ሔደን ፍትህን አናዛባም ሲሉም ተገቢ ፍትህ በመስጠት ለፍትህ መቆማችንን እናረጋግጣለን ሲሉ ገልጸዋል በጽሁፋቸው ።