የ205 ግለሰቦች የባንክ ሒሳብ ታገደ

(ኢሳት ዲሲ–ህዳር 6/2011) የፌደራል ፖሊስ የወንጀል ምርመራ ቢሮ የ205 ግለሰቦች የባንክ ሒሳብ እንዲታገድ አደረገ።

ፌደራል ፖሊስ በቀድሞ የደህንነትና የመከላከያ ሰራዊት ከፍተኛ አመራሮችና ቤተሰቦቻቸው ስም የተከፈቱ የባንክ ሂሳቦች መረጃ እንዲሰጠው በጠየቀው ደብዳቤ በተጠርጣሪዎቹ ግለሰቦች ሚስትና ልጆቻቸው ስም የተከፈቱትን በዝርዝር ገልጿል።

በሌብነት ወንጀል ተጠርጥረው የታሰሩ የሜቴክ ሃላፊዎች ሜጀር ጄነራል ክንፈ ዳኘውን ጨምሮ የ147 ሰዎች የባንክ ሂሳብ በሙስና ተጠርጠረው የባንክ ሂሳባቸው ሲታገድ የአቶ ጌታቸው አሰፋና የ57 ሰዎች የባንክ ሂሳብ ደግሞ ከሰብዓዊ መብት ጥሰት ጋር በተያያዘ አካውንታቸው እንዲታገድ ተደርጓል።

አቶ ጌታቸው በእሳቸውና በሴት ልጃቸው የተከፈቱት የባንክ ሂሳቦች እንዲታገዱና መረጃ እንዲሰጥባቸው ከተጠየቀባቸው ግለሰቦች ዝርዝር ውስጥ ይገኛሉ።

ለሁለት ቀናት ተሰውረው ትላንት የተያዙት የቀድሞ የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽነር አቶ ያሬድ ዘሪሁን በአምስት ልጆቻቸውና ባለቤታቸው ስም የተከፈቱ የባንክ ሂሳቦቻቸው ጭምር መታገዱን ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

ከ58ቱ በሰብዓዊ መብት ጥሰት ወንጀል ምክንያት ከታገዱ የባንክ ሂሳባች ከ40 በላይ የሚሆኑት በሚስት፣ በልጆችና በወንድም ስም የተከፈቱ መሆናቸው ተመልክቷል።

በሌብነት ወንጀል ተጠርጥረው ሂሳባቸው እንዲዘጉ ከተደረጉት 147 የባንክ አካውንቶች ከ80 በላይ የሚሆኑትም በሚስትና ልጆች የተከፈቱ መሆናቸው ታውቋል።

በጠቅላይ አቃቤ ህግ እንዲታገዱ ከተደረጉት የሜቴክና መከላከያ ከፍተኛ አዛዦች መካከል ሜጀር ጄኔራልጄ ክንፈ ድኘው፣ሜጀር ጄኔራል  ብርሃነ ነጋሽ፡ ብርጋዴር ጄኔራል ጠና ቁሩንዲ፣ ብርጋዴ ጄኔራል ብርሃን በየነ፣ብርጋዴር ጄኔራል ሃድጎ ገብረ ጊዮርጊስ እንደሚገኙበት ተገልጿል።