(ኢሳት ዲሲ–ህዳር 5/2011)በመስቃንና ማረቆ ወረዳዎች መካከል በተቀሰቀሰ ግጭት በርካታ ሰዎች መጎዳታቸው ተገለጸ።
በእስካሁኑ ግጭት ከ15 በላይ ቤቶች በእሳት መጋየታቸውም ተሰምቷል።
ይሄ ዜና እስከተጠናቀረበት ድረስ በሃሙስ ገበያ፣በኢንሴሮ ከተሞችና በዙሪያው ባሉ አካባቢዎች ግጭቱ ተባብሶ መቀጠሉን፣ የሰው ሕይወት ማለፉንና በርካታ ቤቶች በእሳት እየተቃጠሉ መሆኑን የኢሳት ምንጮች ገልጸዋል።
ወደ አካባቢው የተላከው ሃይል ቁጥር አነስተኛ መሆንና የግጭቱ ስፋት አለመመጣጠን ለችግሩ መፍትሄ ሊያስገኝ አልቻለም ተብሏል።
ለሁለቱ ወረዳዎች ግጭት መቀስቀስ ምክንያቱ ደኢህዴን በ10ኛ መደበኛ ጉባኤው ያሳለፈው ውሳኔ ነው ይላሉ።
ይሄ ውሳኔ ደግሞ በ44ቱም በወረዳዎች በልማት በመልካም አስተዳደርና በሌሎችም መስኮች የሁሉም የእኩል መብት ተጠቃሚነት እንዲረጋገጥ የሚያደርግ ነው።
ከዚህም ሌላ ህዝብ የበዛባቸውን ወረዳዎችን ለሁለት ለመክፈል በመንግስት በኩል እቅድ ተይዞ ውይይት መደረጉንም ይናገራሉ።ይሄ ውሳኔ ደግሞ በዘር በሃይማኖት የሚፈጸም አይደለም የሚል ነበር።
ይህንንም ውሳኔ አውርዶ ህዝቡን አወያየ ህዝቡም ተቀበለው ይላሉ ነዋሪዎቹ።
ይህንን ውሳኔም ተፈጻሚ ለማድረግም በቡታጅራ አመራሮቹ ስብሰባ እንደነበሩም መረጃውን ያደረሱን ነዋሪዎች ይገልጻሉ።
ነገር ግን ጉዳዩ ያልተዋጠላቸውና በለውጡ የማያምኑ አካላት በፈጠሩት ችግር አካባቢው ለከፋ ቀውስ ተዳርጓል ይላሉ።
እነዚህ አካላት እየተፈጁ ያሉትም ከህዝቡ ጋር ሳይሆን ለውጥን አንግቦ ከመጣው መንግስት ጋር ነው።ይህንን ያልሆነ አካሄዳቸውን ለማስፈጸም ደግሞ በሁለቱ ወረዳዎች መካከል ከባድ ግጭት እንዲፈጠር አድርገዋል ይላሉ።
በዚህ ግጭት እስካሁን ድረስ ጅጋ በሚባል ቀበሌ 4 ሰዎች ለሕይወታቸው በሚያሰጋ መልኩ ተጎድተዋል ብለዋል።
አራቱ ሰዎች ለሕይወት በሚያሰጋ መልኩ መጎዳታቸው ቢገለጽም ከችግሩ ስፋት አኳያ ግን የሞቱትን ሰዎች ቁጥር ማወቅ አለመቻሉን ነው ምንጮቹ የገለጹት።
ወጃ በሚል ቀበሌ ውስጥ አሁንም በከባድ መሳሪያ የታገዘ የተኩስ ልውውጥ እየተደረገ ነው።በዚህም የሰው ሕይወት ማለፉንና ቤቶችም መቃጠላቸውን ነው ለኢሳት የደረሱት መረጃዎች የሚያመለክቱት።
በአካባቢው ያለው ችግር አሁንም እንደቀጠለ ነው የሚሉት የኢሳት የመረጃ ምንጮች ነዋሪው ቤቱን ለቆ ጎዳና ላይ ተበትኗል።
በ50 አመት ታሪክ እንዲህ አይነት ግጭት በአካባቢው ተከስቶ አያውቅም በተባለበት በዚህ ግጭት ነዋሪዎቹ ሚደርሱበት አተው የድረሱልን ጥሪ እያሰሙ መሆኑ ተገልጿል።
ችግሩ በሃሙስ ገበያ፣ኢንሴሮ ከተማና በዙሪያው አካባቢዎች በሙሉ ይሄ ዜና እስከተጠናቀረበት ድረስ ግጭቱ መቀጠሉን፣ቤቶች እየተቃጠሉ መሆኑንና ይሰው ሕይወት ማለፉም ተሰምቷል።
ለችግሩ መፍትሄ ይሰጣል ተብሎ ወደ ስፍራው የደረሰው ሃይልም ቢሆን ከቁጥሩ አነስተኛ መሆንና ከግጭቱ ስፋት አንጻር ምንም መፍትሄ መስጠት አለመቻሉም ተገልጿል።
የተፈጠረውን ችግር በተመለከተ የሚመለከታቸውን አካላት ለማናገር ኢሳት ያደረገው ሙከራ ሊሳካ አልቻለም።