(ኢሳት ዲሲ–ጥቅምት 28/2011) በአሜሪካ በተካሄደው የአማካይ ዘመን ምርጫ ትውልደ ኤርትራዊና ትውልደ ሶማሊያዊ የአሜሪካ ኮንግረስ አባላት ሆነው ተመረጡ።
ለ435 የአሜሪካ ምክር ቤት ወንበር ትውልደ ሶማሊያዊዋ ኢላን ኦማር በአሜሪካ ታሪክ የመጀመሪያዋ ሙስሊም የኮንግረስ አባልም ሆነዋል።
የ34 አመቱ ዮሴፍ ንጉሴ በኤርትራ ውስጥ በሚካሄደው ጦርነት ሳቢያ ቤተሰቦቹ ወደ አሜሪካ ከተሰደዱ በኋላ በኮሎራዶ ግዛት መወለዱን በሕይወት ታሪኩ ላይ ተመልክቷል።
ከኮሎራዶ ግዛት ለኮንግረስ ከተመረጡ አባላት አንዱ በመሆን ከ435 ሕግ አውጪዎች አንዱ ለመሆን የበቃው ትውልደ ኤርትራዊው ዮሴፍ ንጉሴ የሕግ ባለሙያ መሆኑም ታውቋል።
በአሜሪካ በተካሄደው የአሜሪካ አማካይ ዘመን ምርጫ ለ435 የአሜሪካ ምክር ቤት ቦታ በተካሄደው ምርጫ ትውልደ ኤርትራዊው ዮሴፍ ንጉሴና ትውልደ ሶማሊያዊቷ ኢላን ኦማር አባል የሆኑበት የዲሞክራት ፓርቲው የምክር ቤቱን አብላጫ ድምጽ አግኝቷል።
በተጓደሉ የሕግ መወሰኛ ምክር ቤት አባላት መካከል በተካሄደው ምርጫ ውጤት ሪፐብሊካኑ የበላይነታቸውን አስጠብቀዋል።
አንድ የአሜሪካ ምክር ቤት አባል አመታዊ ደሞዙ 174ሺ የአሜሪካ ዶላር መሆኑም ታውቋል።
ይህ በእንዲህ እንዳለም በኔቫዳ ግዛት በተካሄደ የምክር ቤት ምርጫ ትውልደ ኢትዮጵያዊው አሌክሳንደር አሰፋ ማሸነፋቸው ታውቋል።
የ36 አመቷ ሶማሊያዊት ስደተኛ ኢላን ኦማር በሚኒሶታ ግዛት ከመራጮች ውስጥ የ78 በመቶውን ድምጽ በማግኘት በአሜሪካ ታሪክ ምክር ቤቱን ከተቀላቀሉ ሁለት ሙስሊም ሴቶች አንዷ ሆነዋል።
ከእሳቸውም በተጨማሪ አንዲት ፓኪስታናዊት ሙስሊም ከ435ቱ የምክር ቤት ወንበር አንዱን የወሰዱ ሲሆን ሒጃብ በመልበስ ምክር ቤቱን የሚቀላቀሉት ግን ሶማሊያዊቷ ኢላን አማር ናቸው።
በሶማሊያ ውስጥ በተፈጠረው ቀውስ ሳቢያ በኬንያ ደደብ የስደተኞች መጠለያ ጣቢያ ከነቤተሰባቸው በልጅነታቸው ለመቆየት የተገደዱት የ36 አመቷ ኢላን ኦማር እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር በ1995 በ14 አመታቸው ወደ አሜሪካ በስደተኝነት ገብተዋል።
በዚህ አመት የአሜሪካው ሕግ አውጪ ምክር ቤት ኮንግረስ አባል ሆነው ከመመረጣቸው በፊት እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር በ2016 በሚኒሶታ ግዛት የምክር ቤት አባል ሆነው አሸንፈው አገልግለዋል።