የኤርትራው ፕሬዝዳንት ወደ ጎንደር ከተማ ሊሄዱ ነው

(ኢሳት ዲሲ–ጥቅምት 28/2011) የኤርትራው ፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቄ የፊታችን አርብ ጎንደር ከተማ ይገባሉ ተባለ።

ፕሬዝዳንቱ በአማራ ክልል በሚያደርጉት ጉብኝት የክልሉን ርዕሰ ከተማ ባህርዳርን ጨምሮ በሌሎች አካባቢዎችም ጉብኝት እንደሚያደርጉ ተመልክቷል።

ፕሬዝዳንት ኢሳያስ የፊታችን አርብ ጎንደር ሲገቡ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድና የአማራ ክልል ባለስልጣናት አቀባበል እንደሚያደርጉላቸው ተመልክቷል።

ኢትዮጵያና ኤርትራ ለ20 አመታት በጠላትነት የቆዩበት ምዕራፍ ባለፈው ሰኔ በጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አሕመድ የአስመራ ጉብኝት ፍጻሜ ማግኘቱ ይታወሳል።

በሁለቱ ሃገራት መካከል የተደረገውን የሰላም ስምምነት ተከትሎ ፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቄ ሁለት ጊዜ ወደ ኢትዮጵያ ጉዞ ማድረጋቸውም አይዘነጋም።

የኤርትራው ፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቄ የአማራ ክልል ጉብኝት የኢትዮጵያ ጉብኝታቸውን ለሶስተኛ ጊዜ ያደርገዋል።

ፕሬዝዳንት ኢሳያስ በሳምንቱ መጨረሻ ከኤርትራ ቴሌቪዥን ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ የሁለቱ ሃገራት የሰላም ስምምነት ለአካባቢው መረጋጋት የፈጠረውን አስተዋጽኦ ዘርዝረዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ በኤርትራ ላይ የተጣለው ማዕቀብ እንዲነሳ መጠየቃቸውን ተከትሎ የጸጥታው ምክር ቤት የዛሬ ሳምንት ረቡዕ ለ10 አመታት ያህል የዘለቀውን ዕቀባ ያነሳል ተብሎ ይጠበቃል።