(ኢሳት ዲሲ–ጥቅምት 12/2011) የደህንነት ካሜራዎችን ጨምሮ ለዲፕሎማቲክ አገልግሎት በሚል ሰበብ በህገወጥ መንገድ ወደ ሀገር ውስጥ የገባ 20 ሚሊየን ብር የሚያወጣ እቃ መያዙ ተነገረ።
የገቢዎች ሚኒስቴር እንዳስታወቀው በሁለት ስማቸው ባልተጠቀሰ ኤምባሲዎች እና በአንድ ዓለም አቀፍ ተቋም ስም በህገወጥ መንገድ ለዲፕሎማቲክ አገልግሎት በሚል የገቡ እቃዎች ተይዘዋል።
እቃዎቹ ታሽገው በቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ በኩል ሲገቡ መያዛቸውን እና እስካሁንም የአንደኛው ኤምባሲ እቃ ብቻ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴርና የኤምባሲው ተወካዮች በተገኙበት መከፈቱ ነው የተነገረው።
በአንዱ ኤምባሲ ስም የገባው እቃ ሲከፈት 20 ሚሊየን ብር የሚያወጡ የደህንነት ካሜራዎች፣ ስማርት ሰዓቶች፣ የመኪና መለዋወጫዎች እና ባለ 65 ኢንች በርካታ ቴሌቪዥኖች ተይዘዋል።
የቀሪውን ኤምባሲ እና ዓለም አቀፍ ተቋም እቃዎች በተመሳሳይ መልኩ ለመክፈት ዝግጅት እየተደረገ ይገኛል ተብሏል።
ገቢዎች ሚኒስቴር የኤምባሲዎቹን እና ዓለም አቀፍ ተቋሙን ማንነት ከመግለፅ ተቆጥቧል።