ታዋቂው የማሲንቆ ተጫዋች ለገሠ አብዲ የቀብር ስነስርአት ተፈፀመ

(ኢሳት ዲሲ–ጥቅምት 12/2011)በኦሮምኛ ሙዚቃ ታዋቂው የማሲንቆ ተጫዋች ለገሠ አብዲ  የቀብር ስነስርአት ዛሬ ተፈፀመ።

የአርቲስቱ የቀብር ስነስርአት በቅድስት ስላሴ ካቴድራል ቤተክርስቲያን ሲፈጸም ቤተሰቦቻቸው፣ ወዳጅ ዘመዶቻቸው እና አድናቂዎቻቸው ተገኝተዋል።

አንጋፋው የኦሮምኛ ማሲንቆ ተጫዋች ለገሠ አብዲ በ1927 ዓ.ም በኦሮሚያ ክልል ሰላሌ ያያ ቃጫማ በተባለ ስፍራ ነው የተወለዱት።

በኦሮምኛ የሙዚቃ አድማጮች የማሲንቆው ንጉስ ተብለው የሚጠሩት ለገሰ አብዲ በሀገር ፍቅር፥ በብሄራዊ ቴአትር፣ በአዲስ አበባ ከተማ ቴአትርና ባልህ አዳራሽ፣ በፖሊስ ኦርኬስትራ፣ በክብር ዘበኛ እንዲሁም በሂልተን ሆቴል የሙዚቃ ስራዎቻቸውን ሲያቀርቡ ቆይተዋል።

ከስልሳ ዓመታት በላይ በማሲንቆ የኦሮምኛን ሙዚቃ ሲጫወቱ የነበሩት ለገሰ አብዲ የኦሮሚኛን ሙዚቃን ቀደም ባሉት ጊዜት ወደ መድረክ በማምጣት ከፍተኛ ሚና ነበራቸው።

አርቲስት ለገሰ ከሚታወቁባቸው የኦሮምኛ ዘፈኖች መካከል ያ ቦና ያቦና፣ ጂጂቱ፣ ኢያ ሀንዳቆ እና ኮቱ ያ ጂጋኮ ተጠቃሽ ናቸው።

ባለፈው ቅዳሜ ሌሊት ከዚህ አለም በሞት የተለዩት ለገሠ አብዲ የቀብር ስነስርአታቸው በዛሬው እለት በቅድስት ስላሴ ካቴድራል ቤተክርስትያን ተፈጽሟል።

አርቲስት ለገሰ አብዲ የአራት ወንዶችና የሶስት ሴት ልጆች አባት ነበሩ፡፡