(ኢሳት ዲሲ–ጥቅምት 12/2011)የኦጋዴን ብሔራዊ ነጻነት ግንባር /ኦብነግ/ ወደ ሃገር ቤት ገብቶ በሰላማዊ መንገድ ለመታገል ከመንግስት ጋር መስማማቱ ተገለጸ።
የኦጋዴን ብሔራዊ ነጻነት ግንባርና የኢትዮጵያ መንግስት ስምምነት ላይ የደረሱት በኤርትራ አስመራ መሆኑም ተመልክቷል።
በውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ወርቅነህ ገበየሁና በኦብነጉ ሊቀመንበር አድሚራል ሙሐመድ ኡመር ኡስማን መካከል የተደረሰውን ስምምነት ተከትሎ የኦብነግ መሪዎች በቅርቡ ወደ ኢትዮጵያ ይመለሳሉ ተብሎ ይጠበቃል።
በ1983 የሽግግሩ መንግስት መስራች የነበረውና እንደ ኦነግ ሁሉ በሽግግር መንግስቱ ሶስት የምክር ቤት ወንበሩን አጥቶ የተባረረው የኦጋዴን ብሔራዊ ነጻነት ግንባር/ኦብነግ/ ከሩብ ክፍለ ዘመን በላይ በትጥቅ ትግል ውስጥ ቆይቷል።
ኢትዮጵያ ውስጥ የመጣውን ለውጥ መሰረት በማድረግ እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር ነሐሴ 12/2018 የተናጠል ተኩስ አቁም በማድረግ ልኡካኑን ወደ ኢትዮጵያ መላኩም ይታወሳል።
እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር በ1984 የተመሰረተው የኦጋዴን ብሔራዊ ነጻነት ግንባር /ኦብነግ/ከ7 አመታት የትጥቅ ትግል በኋላ በ1983 ከሽግግር መንግስቱ መስራች ድርጅቶች አንዱ ነበር።
ከስርአቱ ጋር ግጭት ውስጥ በመግባቱም ተመልሶ መሳሪያውን በማንሳት ለ27 አመታት በአጠቃላይ ለ34 አመታት የትጥቅ ትግል ሲያካሂድ የቆየ ድርጅት ነው።
አሁን በሰላማዊ መንገድ ለመታገል ትላንት አስመራ ላይ ስምምነት የፈረመው ኦብነግ ከሌሎች የኢትዮጵያ ሃይሎች ጋር በትብብር መስራት መጀመሩም ይታወሳል።
በግንቦት ወር 2009 ከአርበኞች ግንቦት 7 ጋር ጀርመን ላይ ትብብር መፍጠራቸው ይታወሳል።
ነፍጥ ካነሱ ዋነኛ የተቃውሞ ሃይሎች አንዱ ከሆነው ኦብነግ በፊት አርበኞች ግንቦት ሰባትና ኦነግ በተመሳሳይ በሰላማዊ መንገድ ለመታገል ወደ ሃገር ቤት መመለሳቸው ይታወሳል።
ኦነግ ትጥቅ በመፍታት ዙሪያ ከመንግስት ጋር የጀመረው ውዝግብ ዕልባት አለማግኘቱም ይታወቃል።