አትሌት ፈይሳ ሌሊሳ አዲስ አበባ ገባ

(ኢሳት ዲሲ–ጥቅምት 12/2011)አትሌት ፈይሳ ሌሊሳ ከሁለት አመታት ስደት በኋላ ትላንት አዲስ አበባ ገባ።

ከጸጥታ ጋር በተያያዘ እንደሆነ በታመነ መልኩ ሕዝባዊ አቀባበል አልተደረገለትም።

ወደ ሃገር የመመለሻ ጊዜው ጭምር ሲለዋወጥበት የቆየው አትሌት ፈይሳ ሌሊሳ ቦሌ አለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ሲደርስ የመንግስት ባለስልጣናት፣ቤተሰቦቹ እንዲሁም አትሌቶች ተቀብለውታል።

በብራዚል ሪዮ ኦሎምፒክ በነሐሴ ወር 2008 በማራቶን ለኢትዮጵያ የብር ሜዳሊያ ያስገኘው አትሌት ፈይሳ ሌሊሳ በኢትዮጵያ ውስጥ የሚካሄደውን አፈና በይበልጥም ግድያውን በመቃወም ስርአቱን በኦሎምፒክ መድረክ መቃወሙ ይታወሳል።

ከሁለት አመት በፊት በብራዚል ሪዮ ኦሎምፒክ ለኢትዮጵያ ሜዳሊያ ያስገኘው ሆኖም በስደት ከብራዚል ወደ አሜሪካ ያቀናው አትሌት ፈይሳ ሌሊሳ በኢትዮጵያ የሚገኙት ባለቤቱና ልጆቹንም ወደ አሜሪካ መውሰዱ ይታወሳል።

ላለፉት 2 አመታት ከሁለት ወር ያህል በስደት የቆየው ጀግናው አትሌት ፈይሳ ሌሊሳ አዲሰ አበባ ሲገባ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ዶክተር ወርቅነህ ገበየሁና የገንዘብ ሚኒስትሩ አቶ አሕመድ ሽዴ ተቀብለውታል።

ጀግናዋ አትሌት ደራርቱ ቱሉን ጨምሮ ሌሎች አትሌቶች እንዲሁም የኦሎምፒክ ኮሚቴ ፕሬዝዳንት ዶክተር አሸብር ወልደጊዮርጊስ እንዲሁም ቤተሰቦቹ በአቀባበል ስነስርአቱ ላይ ተገኝተዋል።

አትሌት ፈይሳ ሌሊሳ በመስከረም ወር 2011 ኢትዮጵያ ሲገባ ደማቅ አቀባበል እንደሚደረግለት መርሃ ግብር ከተያዘለት በኋላ ከጸጥታ ችግር ጋር በተያያዘ የመመለሻ ቀኑ መራዘሙ ተመልክቷል።

የመምጫው ቀን በይፋ ሳይገለጽም ትላንት ጥቅምት 11/2011 አዲስ አበባ ካባለቤቱና ከ2 ልጆቹ ጋር ገብቷል።

ወላጆቹም በአቀባበል ስነስርአቱ ላይ እንደነበሩም ታውቋል።