(ኢሳት ዲሲ–መስከረም 30/2011) በአዋሳ ከተማ የሚገኘው አሮጌው ገበያ ሙሉ በሙሉ በሚባል መልኩ ወደመ።
በገበያው የተነሳውን እሳት ለማጥፋት የከተማው ማዘጋጃ ቤት የእሳት አደጋ ሰራተኞች በስፍራው የደረሱት እሳቱ ከተነሳ ከ1 ሰአት ተኩል በኋላ መሆኑም ታውቋል።
ከአዋሳ ከተማ መቆርቆር ጋር አብሮ እንደተመሰረት የሚነግርለት ገበያ በከተማው አዲስ የገበያ ስፍራ በመመስረቱ አሮጌው ገበያ በመባል ይጠራል።
በዚህ ስፍራ ለረጅም ዘመናት በንግድ ስራ የተሰማሩ የከተማው ነዋሪዎች ሀብት ንብረት አፍርተው ኖረዋል።
እድሜ ልክ ያፈሩትን ንብረት ግን በአንድ ሌሊት ማጣታቸው ትልቅ ሀዘን ሆኖባቸዋል።
እሳቱ ከምሽቱ አንድ ሰኣት አካባቢ ከፍራሽ ተራ እንደተናሳ የተገለጸ ሲሆን ፣ ልብስና ጫማ መሸጫ መደብሮች በተለምዶ ታይዋን ተራ፣ጥራጥሬ መሸጭ፣የባህል አልባሳት መሸጫ፣ አትክልት ተራ መደበሮች ሙሉ በሙሉ መውደማቸው ታውቋል።
የወደመው ንብረት ግምቱ ምንያህል እንደሆን ነዋሪዎች በዚህ ሰዓት ማወቅ እንዳልቻሉ ተናግረዋል።
የከተማው ነዋሪዎች ለኢሳት እንደገለጹት የከተማው ማዘጋጃ ቤት እሳቱን ለማጥፋት ያደረገው ሙከራ እጅግ ደካማ እንደነበር ገለጸዋል።
ጨምረውም የእሳት አደጋ ባለሙያዎቹ አደጋው ከደረሰ በኋላ የተገኙት ከተለያዩ መጠጥ ቤቶች ሲሆን በወቅቱም ሰክረው እንደነበር ጠቅሰዋል።
ከዚህ በተጨማሪም ለእሳት አደጋው ወደተከሰተበት ቦታ ለመሄድ ለእሳት አደጋ መከላከያው መኪና ነዳጅ ለመቅዳት የሄዱት እሳቱ ከተነሳ ከአንድ ሰዓት ከሰላሳ ደቂቃ በኋላ መሆኑንም አክለዋል።
የእሳት አደጋ መኪናው ወደ ስፈራው ሲድርስም ከህዝቡ ከፍተኛ ተቃውሞ ገጥሞት በድንጋይ መሰባበሩ እና በቦታው የደረሰውም አምቡላንስ በነዋሪው ጥቃት እንደተሰነዘረበት ለማወቅ ተችሏል።
በዚህም የተነሳ የገበያው አብዛኛው ክፍል መሉ በሙሉ መውደሙን ነዋሪዎቹ በሀዘን ይናገራሉ ።
ጨምረውም እሳቱ እስከዛሬ ሙሉ ለሙሉ አለመጥፋቱን ተናግረዋል።
የአዋሳ ከተማ ከ300 ሺ በላይ ነዋሪ ይኖርባታል ተብሎ ይገመታል።
ነገር ግን ከከተማው እድገት ጋር የሚመጣጠን የእሳት አድጋ ብርጌድ እንደሌለ ነዋሪዎች በመሬት ተናግረዋል።
ይህንን ሁኔታ ለማጣራት ወደ ሃዋሳ ከተማ አስተዳደርና ማዘጋጃን ቤት ስልክ ደውለን ያደረግነው ሙከራ ለጊዜው አልተሳካም።