መንግስት ኦነግን ትጥቅ ያስፈታል ተባለ

(ኢሳት ዲሲ–መስከረም 30/2011) መንግስት የዜጎችን ደህንነት ለማስጠበቅ ሲል ኦነግን ትጥቅ ለማስፈታት እንደሚገደድ የኢትዮጵያ መንግስት አስታወቀ።

የመንግስት ኮሚኒኬሽን ጉዳዮች ሚኒስትር ድኤታ አቶ ካሳሁን ጎፌ ዛሬ በሰጡት መግለጫ መንግስት የታጠቁ ሃይሎች በሃገር ውስጥ እንዲንቀሳቀስ በማድረግ ሁለት መንግስት እንዲኖር አይፈቅድም ብለዋል።

ሰላማዊ የፖለቲካ ትግል ለማድረግ የወሰነ ሃይል በመሳሪያ ጭምር እንደማይንቀሳቀስ የገለጹት የመንግስት ኮሚኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት ሃላፊ ኦነግ ትጥቅ ለመፍታት አልተስማማንም የሚለውን አቋሙን እንዲመረምር የአፍ ወለምታም ከሆነ ይህንኑ እንዲያርም ጥሪ አቅርበዋል።

የኦሮሞ ነጻነት ግንባር ወደ ሃገር ቤት ሲገባ በቦሌም ሆነ በዛላ አምበሳ የገቡት አባላትና አመራሮቹ ያለትጥቅ መግባታቸውን ያስታወሱት የመንግስት ኮሚኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት ሃላፊ አቶ ካሳሁን ጎፌ የትኛውም የፖለቲካ ሃይል መሳሪያ ይዞ እንዲንቀሳቀስ እንደማይፈቀድም አስታውቀዋል።

የተመለሱት የኦነግ ወታደሮች በመንግስት እጅ ሆነው በስልጣን ላይ መሆናቸውንም አመልክተዋል።

ሌሎች ትጥቅ ያልፈቱትን ኦነግ ትጥቅ እንዲያስፈታ ጥሪ ያቀረቡት የመንግስት ኮሚኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት ሃላፊ ኦነግ ሃላፊነቱን ካልተወጣ መንግስት የህዝቡን ደህንነት ለማስጠበቅ ትጥቅ የማስፈታቱን ርምጃ እንደሚወስድ አሳስበዋል።

የኦሮሞ ነጻነት ግንባር/ኦነግ/ የሚሰጣቸው መግለጫዎች እርስ በርስ የተምታቱ መሆናቸውን ያስታወሱትና ዛሬ አዲስ አበባ ላይ መግለጫ የሰጡት የመንግስት ኮሚኒኬሽን ጉዳዮች ሃላፊ ትጥቅ ስለመፍታት የሰጠውን መግለጫ መልሶ እንዲያጤነው አሳስበዋል።

የአፍ ወለምታም ከሆነ እርምት እንዲደረግበት ጥሪ አቅርበዋል።

የመንግስት ትዕግስት መልፈስፈስ ተደርጎ መወሰድ የለበትም ያሉት የኮሚኒኬሽን ጉዳዮች ሚኒስትር ዴኤታው አቶ ካሳሁን ጎፌ ኢትዮጵያ በጦር ሃይል ከአፍሪካ አምስት ግንባር ቀደም ሃገራት አንዷ መሆንዋንም አስታውሰዋል።

ኦነግም ሆነ ማንም ሃይል አሸንፎ እንዳልገባም መታወቅ ይኖርበታል ሲሉ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።