(ኢሳት ዲሲ–መስከረም 24/2011)ከኢትዮጵያ የተለያዩ ስኳር ፋብሪካዎች ለስኳር ልማት ፈንድ ተብሎ የተሰበሰበው 65 ቢሊየን ብር ያህል ገንዘብ የትና ለምን አላማ እንደዋለ እንደማይታወቅ አንድ የመስኩ ባለሙያ ገለጹ።
ወንጂ ስኳር ፋብሪካ የፋክተሪና ሎጅስቲክ ስራ አስኪያጅ የነበሩት አቶ አማረ ለገሰ ከኢሳት ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ እንደተናገሩት ገንዘቡ ለ22 አመታት ያህል የተሰበሰበ ነው
ስኳር ከፋብሪካ በሚወጣበት ዋጋና ለነጋዴዎች በሚደርሰው ሒሳብ በትንሹ በኩንታል የአንድ ሺህ ብር ልዩነት እንደነበረው ያስታወሱትና የወንጂ ስኳር የፋክተሪና ሎጅስቲክ ስራ አስኪያጅ የነበሩት አቶ አማረ ለገሰ ከእያንዳንዱ ኩንታል የሚሰበሰበው አንድ ሺ ብርና ከዚያ በላይ የሆነ የገንዘብ መጠን አመታዊ ሒሳብ 3 ነጥብ 2 ቢሊየን ብር ያህል መሆኑንም ገልጸዋል።
በገበያ ላይ በኩንታል እስከ 1 ሺ 800 ብር የሚሸጠው ስኳር ከፋብሪካው ከ250 እስከ 300 ብር ብቻ መሸጡን በመቃወም የሰራተኛ ማህበራት መሪዎችና ሰራተኞች ሲንቀሳቀሱ ገንዘቡ ሌላ የስኳር ፋብሪካ ለመገንባት የሚውል ነው ተብሎ መልስ ይሰጥ እንደነበርም አስታውሰዋል።
ሆኖም አዳዲስ ስኳር ፋብሪካዎቹ ሲገነቡ በዚህ ገንዘብ ሳይሆን ከውጭና ከሃገር ውስጥ በሚገኝ ብድር መሆኑንም ገልጸዋል።
በዚህ መልክ ለ22 አመታት የተሰበሰበው ገንዘብ ከ65 ቢሊየን ብር በላይ መሆኑንም አቶ አማረ ለገሰ ከኢሳት ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ ገልጸዋል።ገንዘቡ የት እንደገባ እንደማይታወቅ በመግለጽም ጭምር።