የኦነግ ታጣቂዎች ትጥቅ አልፈቱም ተባለ

(ኢሳት ዲሲ–መስከረም 24/2011) የኦሮሞ ነጻነት ግንባር/ኦነግ/ ታጣቂዎች በተለያዩ የኦሮሚያ አካባቢዎች ትጥቅ አለመፍታታቸውን አንድ ከፍተኛ የኦነግ አመራር ገለጹ።

የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስትም ኦነግ በገባው ቃል መሰረት ታጣቂዎቹን ወደ ካምፕ እንዲያስገባም ጥሪ አቅርቧል።

የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት የገጠር አደረጃጀት ሃላፊና የኦዴፓ ስራ አስፈጻሚ አቶ አዲሱ አረጋ “በኦነግ ስም ታጥቀው በኦሮሚያ አንዳንድ አካባቢዎች የሚንቀሳቀሱትን በትዕግስትና በብስለት እያየን ነው” በማለት ከሰሞኑ ያስተላለፉትን መልዕክት ተከትሎ የኦነግ ከፍተኛ አመራር ምላሽ ሰጥተዋል።

የኦሮሞ ነጻነት ግንባር/ኦነግ/ አመራር የሆኑት አቶ ቶሌራ አደባ አዲስ አበባ ላይ ለንባብ ለበቃው ለሪፖርተር ጋዜጣ በሰጡት ቃለ ምልልስ ትጥቅ ያልፈቱ የኦነግ ወታደሮች መኖራቸውን አረጋግጠዋል።

በሰሜን፣በምስራቅ፣በመካከለኛውና በደቡባዊ የኦሮሚያ ክልል የታጠቁ ወታደሮቻችን አሉ ያሉት አቶ ቶሌራ አዳባ “ወታደሮቹን ትጥቅ ለማስፈታት ከመንግስት ጋር እየሰራን ነው”ብለዋል።

በምስራቅ ወለጋ 4 የካማሼ ዞን ባለስልጣናት መገደላቸውን ተከትሎ በቤንሻንጉል ክልል በተወሰደ የአጸፋ ጥቃት ከ40 በላይ ሰላማዎ ሰዎች ሲገደሉ 100 ሺ የሚጠጉ የኦሮሞና የአማራ ተወላጆች መፈናቀላቸው ይታወቃል።

4ቱን የቤንሻንጉል ክልል ባለስልጣናት ማን እንደገደለ ግን በይፋ የተገለጸ ነገር የለም።