የቀድሞው የሶማሌ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አብዲ ሙሃመድ እና ግብረ አበሮቻቸው ላይ ተጨማሪ የአስር ቀናት የምርመራ ጊዜ ተሰጠ።
( ኢሳት ዜና መስከረም 18 ቀን 2011 ዓ/ም ) ባለፈው ዓመት ነሃሴ ወር 2010 ዓ.ም በሶማሌ ክልል ውስጥ የተፈጸመውን ኢሰብዓዊ የመብት ጥሰትን በቀዳሚነት ሲመሩት ነበሩ ተብለው ተጠርጥረው በቁጥጥር ስራ የዋሉት የክልሉ የቀድሞ አስተዳዳሪ የነበሩት አቶ አብዲ መሀመድ እና አራት የክልሉ ባለስልጣናት ፍርድ ቤት ቀርበው ተጨማሪ የአስር ቀናት የጊዜ ቀጠሮ ተፈቀደ።
በጅጅጋና አካባቢው ለተፈጸመው በብሄር እና ሃይማኖት ላይ ላነጣጠሩ የጅምላ ጭፍጨፋ ወንጀሎችን ለማጣራት መርማሪ ፖሊስ በተፈቀደለት የ14 ቀናት ቀነ ቀጠሮ ወቅት ከወንጀሉ ጋር ተያያዥ ያላቸውን ምርመራዎች ሲያደርግ መቆየቱን ለችሎቱ ገልጿል። የ41 ምስክሮች ቃል መቀበሉን፣ የተዘረፈውን ንብረት ግምት እንዲሁም በሄጎ እና በልዩ ኃይሉ የተጨፈጨፉ ሰዎች አስክሬን ምርመራ ውጤት መረጃን ጨምሮ የ18 ሟቾችን እና የ438 አካል ጉዳት የደረሰባቸውን ግለሰቦች የህክምና ማስረጃ መሰብሰቡንና ዘጠኝ የጦር መሳሪያዎችን በቁጥጥር ስር ማዋሉን ለችሎቱ አብራርቷል፡፡
በተጨማሪም የፍርድ ቤት ማዘዣ የወጣባቸውን ግብረአበሮች መያዝ፣ በአንድ ጉድጓድ ውስጥ የተቀበሩ ሰዎች ማንነትን መለየት፣ የአስገድዶ መድፈር የተፈጸመባቸውን ሴቶች መለየት፣ የሕክምና መስረጃ ማሰባሰብ፣ የተደበቀ የጦር መሳሪያና ገንዘብ ማሰባሰብ፣ የምስክር ቃል ለመቀበል የተሰጠው የምርመራ ጊዜ በቂ ባለመሆኑ ተጨማሪ የ14 ቀናት የምርመራ ጊዜ እንዲሰጠው መርማሪ ፖሊስ ፍርድ ቤቱን ጠይቋል።
ተጠርጣሪዎቹ መርማሪ ፖሊስ የጠየቀውን የ14 ቀናት የምርመራ ጊዜ ተገቢነት የለውም፣ አቀራረቡ በዝርዝር አይደለም፣ ተገቢውን ህክምና እንድናገኝ አልተደረግንም። በእስር ቤቱ አያያዝ በኩል ችግር በመኖሩ ፍርድ ቤቱ የምርመራ መዝገቡ ሊለያይልን ይገባል። ሲሉ ቅሬታቸውን አሰምተዋል።
መርማሪ ፖሊሰ በበኩሉ ምርመራው በዝርዝር ቅርቧል። ተጠርጣሪዎች በክልሉ የተፈጸመውን የብሔርና የሃይማኖት ግጭት ጅምላ ጭፍጨፋ የዜጎች መፈናቀልና የንብረት ውድመት በቅንጅት በመስራታቸው ምርመራው ተነጣጥሎ ሊታይ አይገባውም።
የሴቶችና የህፃናት ጉዳዮች ሃላፊ ወ/ሮ ራሂማ መሀመድና የዲያስፖራ ቢሮ ኃላፊው አቶ አብዱልራዛቅ ሳኒ ግጭቱን በፌስ ቡክ ሲቀሰቅሱ ነበር። የፖሊስ ኮሚሽነር የነበሩት አቶ ፈሪሃን ጣሂር ሂጎዎችን መሳሪያ አስታጥቀው ዜጎችን አስጨፍጭፈዋል። ልዩ ኃይሎችንም ለጥፋት በማነሳሳት ግጭቱን በመኪና እየዞሩ ያጠናከሩና በርካታ ታራሚዎችን ከማረሚያ ቤት አስወጥተው በጭካኔ አስረሽነዋል᎓᎓ ምርመራው ሰፊ እና ውስብስብ በመሆኑ መርማሪ ቡድኑ የዋስትና መብት አሊያሰጣቸው አይችልም። ሲል መርማሪ ቡድኑ ተከሳሾቹ ጉዳያቸው በተናጠል እንዲታይ ያቀረቡትን አቤቱታ ተቃውሟል።
የፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ተረኛ ወንጀል ችሎት መርማሪ ፖሊስ ያቀረበውን የ14 ቀናት የምርመራ ጊዜ ውድቅ በማድረግ የ10 ቀንናት ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ በመፍቀድ ለመስከረም 28 ቀን 2011 ዓ.ም ተለዋጭ የጊዜ ቀጠሮ ሰጥቷል።