ብአዴን ነባር አመራሮችን በአዳዲስ አመራሮች የመተካት ስራ ይሰራል ብለው እንደሚጠብቁ አባሎቹ ገለጹ

ብአዴን ነባር አመራሮችን በአዳዲስ አመራሮች የመተካት ስራ ይሰራል ብለው እንደሚጠብቁ አባሎቹ ገለጹ
( ኢሳት ዜና መስከረም 18 ቀን 2011 ዓ/ም ) የብአዴን አባላት ለኢሳት እንደገለጹት ድርጅቱ በክልሉ ብቻ ሳይሆን በአገር አቀፍ ደረጃ በተለይም በአገሪቱ እየተካሄደ ያለውን የለውጥ እንቅስቃሴ ከዶ/ር አብይ አህመድ ጋር በመሆን ወደ ፊት ለማስኬድ ከባድ ሃላፊነት የተጣለበት በመሆኑ፣ ይህንኑ ሃላፊነት በብቃት ለመወጣት የሚያስችለውን አመራር ይመርጣል የሚል እምነት አላቸው። በጉባኤው ላይ የድርጅቱ ሊ/መንበርና ም/ል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን እና የአብዴን ምክትል ሊመንበርና የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ገዱ አንዳርጋቸው ባቀረቡዋቸው ንግግሮች ላይ ድርጅቱ በወጣት አመራሮች እንደሚመራ መግለጻቸው ተስፋቸውን አለምልሞታል።
የድርጀቱ ሊቀመንበርና ምክትል ሊቀመንበሩ በሃላፊነት ቦታቸው ላይ ይቀጥሉ አይቀጥሉ በውል የታወቀ ነገር የለም። ይሁን እንጅ አቶ ደመቀ መኮንን በተደጋጋሚ የስልጣን መልቀቂያ ጥያቄ አቅርበው ተቀባይነት ባለማግኘታቸውና በአሁኑ ጉባኤ የመጨረሻ ውሳኔ እንደሚሰጣቸው ቀደም ብሎ ስምምነት ያለ በመሆኑ፣ ስልጣናቸውን የሚለቁበት እድል ከፍተኛ ሊሆን ይችላል። ኦህዴድ፣ ደኢህዴንና ህወሃት መሪዎቻቸውን ሲቀይሩ ብአዴን መሪውን እስካሁን ሳይቀይር ቆይቷል።
ኢትዮጵያ በከፍተኛ የለውጥ ማዕበል ትመታ በነበረበት ወቅት፣ አገሪቱ ሰላማዊ የስልጣን ሽግግር እንድታደርግ፣ በስልጣን ተዋረድ ጠ/ሚኒስትር መሆን ይችሉ የነበረ ቢሆንም፣ ቦታውን “ለአዲስ አመራር መልቀቅ አለብኝ” በሚል ራሳቸውን ከውድድር አርቀው ጠ/ሚኒስትር አብይ አህመድ እንደሚረጡ ከፍተኛ ስራ መስራታቸውን ጉዳዩን በቅርብ የሚያውቁ ሰዎች ይናገራሉ። ከቀድሞው ጠ/ሚኒስትር ሃይለማርያም ደሳለኝ ጋር አብረው ስልጣን ለመልቀቅ ፍላጎት የነበራቸው አቶ ደመቀ፣ ጥያቄያቸው ተቀባይነት ባለማግኘቱ እስካሁን ድረስ በስልጣን ላይ ቆይተዋል።
ብአዴን ጠንካራ ድርጅት ሆኖ እንዲወጣ ከፍተኛ ሚና እንደተጫወቱ የሚነገርላቸው አቶ ደመቀ፣ ሰሞኑን በእርሳቸው ላይ ይነዙ ስለነበሩ አሉባልታዎች በክልሉ ቴሌቪዥን ቀርበው መልስ ሰጥተዋል። በተለይም የኢትዮጵያን መሬት ለሱዳን አሳልፈው እንደሰጡ ተደርጎ ይወራባቸው የነበረው ወሬ ሃሰት መሆኑን በአጽንዖት የተናገሩት አቶ ደመቀ፣ የኢትዮጵያ መሬት ለሱዳን ያላግባብ መሰጠቱን ካወቁ በሁዋላ ብአዴንና ፌደራል መንግስት መሬቱ እንዲመለስ ጥረት እንደሚያድርጉ ገልጸዋል።
በድርጅቱ 12ኛ ጉባኤ ላይ ያቀረቡትን ንግግር ተከትሎ በማህበራዊ ሚዲያ ድጋፍ እየተቸራቸው የሚገኙት አቶ ደመቀ በእርሳቸው ቦታ ሌሎች አመራሮች እንዲተኩ የድርጅቱን ከፍተኛ አመራሮች እየወተወቱ ሲሆን፣ የድርጅቱ አመራሮችም ጥያቄውን የመቀበል አዝማሚያ እየያዙ በመምጣታቸው አቶ ደመቀ በሌላ አመራር ሊተኩ ይችላሉ። አቶ ደመቀ ስልጣን የሚለቁ ከሆነ፣ የኢህአዴግ ምክር ቤት መስከረም 25 በአዋሳ በሚያደርገው ጉባኤ ላይ ምክትል ጠ/ሚኒስትሩን ይሰይማል።
የክልሉ ፕሬዚዳንት አቶ ገዱ አንዳርጋቸው ከነባር ወደ አዲስ አመራር የሚደረገውን ሽግግር ስርዓት ለማስያዝ ሲባል በስልጣን ላይ ሊቆዩ ይችላሉ።
በሌላ በኩል ደግሞ ደኢህዴን እያደረገ ባለው 10ኛ ጉባኤ አዳዲስ አመራሮች ወደ ፊት እንደሚመጡ የድርጅቱ ሊ/መንበር ወ/ሮ ሙፈሪያት ካሚል ገልጸዋል።
በክልሉ ህዝብን ከህዝብ የማጋጨት ሴራዎችን እየተስተዋሉ መሆኑን የገለጹት ወይዘሮ ሙፈሪያት፣ የህግ የበላይነት እንዲረጋገጥ መስራት እንደሚገባም ገልጸዋል።