የኢሬቻ በዓል ከፖለቲካ በራቀ ባህላዊና ትፊቶችን በሚያንጸባርቅ መልኩ እንዲከበር ሲሉ የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ለማ መገርሳ አሳሰቡ።
( ኢሳት ዜና መስከረም 18 ቀን 2011 ዓ/ም ) በቢሾፍቱ ሆራ አሰርዲ ሃይቅ በየዓመቱ የሚከበረውን የኢሬቻ ምስጋና በዓልን አስመልክቶ የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ለማ መገርሳ ለበዓሉ ተሳታፊዎች የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክታቸውን ጨምሮ ስለ በዓሉ አከባበር ማሳሰቢያ ሰጡ።
”በኦሮሞ ህዝብ ዘንድ ትልቅ ስፍራ ለሚሰጠው የኢሬቻ በዓል እንኳን አደረሳችሁ!” ያሉት አቶ ለማ መገርሳ የዘንድሮው ዓመት የኢሬቻ በዓል ካለፈው ዓመት በተሻለ ሁኔታ ሰላማዊ በሆነ መልኩ እንዲከበር የበዓሉ ታዳሚያንን ጨምሮ የሚመለከተው ሁሉ የበኩሉን ዽርሻ እንዲወጣ ጥሪ አቅርበዋል። በተለይም አባ ገዳዎች፣ ወጣቶች እና ሁሉም የኅብረተሰብ ክፍሎች ባህልን በሚያፅባርቅ መልኩ የኢሬቻን በዓል አንዲያከብሩም ጠይቀዋል።
በዓሉን ለማክበር ወደ ስፍራው የሚሄዱ በሙሉ ከፖለቲካ ፓርቲ ዓርማ፣ ባንዲራ እና ዘፈኖች ራሳቸውን እንዲቆጥቡ ሲሉም አሳስበዋል። የኢሬቻ በዓል የገዳ ስርዓት ነፀብራቅ በመሆኑ ልክ እንደ ገዳ ስርዓት ሁሉ የኢሬቻ በዓልንም በዩኔስኮ የዓለም ቅርስነት ለማስመዝገብ በመንግስት በኩል እየተሰራ ነውም ብለዋል።
በበዓሉ አካባቢ የጤና ችግሮች ቢያጋጥሙ አፋጣኝ እገዛ የሚሰጡ የጤና ባለሙያዎች አስቀድመው ቅድመ ዝግጅታቸውን ማጠናቀቃቸውን አቶ ለማ መገርሳ አክለው ገልጸዋል።