(ኢሳት ዲሲ–መስከረም 2/2011) በዩናይትስ ስቴትስ አሜሪካ ምስራቃዊ ክፍል ላይ ያንዣበበው ዝናብ የቀላቀለ ከፍተኛ አውሎ ንፋስ ከ1 ነጥብ 5 ሚሊየን በላይ ሰዎችን ማፈናቀል ጀመረ።
የፌደራል መንግስቱ አስፈላጊ ድጋፍ እንደሚያደርግ ፕሬዝዳንት ትራምፕ ቃል የገቡ ሲሆን ከሩብ ክፍለ ዘመን ወዲህ በአይነቱ አደገኛው አውሎ ንፋስ መሆኑም ተመልክቷል።
ፍሎረንስ የሚል ስያሜ የተሰጠው ይህ አውሎ ንፋስ በሰአት 130 ማይል እየበረረ እንደሚጓዝ ተገምቷል።
በዩናይትድ ስቴትስ አሜሪካ ምስራቃዊ ክፍል አንዣቧል የተባለውና በከፍተኛ ዝናብ የሚታጀበው አውሎ ንፋስ የሰሜንና ደቡብ ካሮላይና እንዲሁም የቨርጂኒያን ግዛት በዋናነት እንደሚያጠቃም ተመልክቷል።
የሃይል መቋረጥ፣የመሰረተ ልማት ውድመትና በፍርስራሽና ጎርፍ የመንገድ መዘጋት ያስከትላል የተባለው ዝናብ የቀላቀለው አውሎንፋስ የአሜሪካ መገናኛ ብዙሃን አብይ ርዕስና የነዋሪው ደግሞ ዋና ስጋት ሆኖ ቀጥሏል።
የጉዳዩን አሳሳቢነት በተመለከተ መግለጫ የሰጡት የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ፣”በምግብ፣በመድሃኒትና በሚያስፈልገው ሁሉ ሰለባዎቹን ለመታደግ በበቂ ተዘጋጅተናል” ብለዋል።
በአደጋው አካባቢ የሚኖሩ ዜጎችም ራሳቸውን ያዘጋጁ ሲሉ መልዕክት አስተላልፈዋል።
እግዚአብሔር ከጎናቸው እንዲሆንም ተመኝተዋል።
በአደጋው ይጠቃሉ ተብለው በተሰጋባቸው ቦታዎች 8 ሚሊየን የታሸጉ ምግቦችና ውሃዎች ተልከዋል።
ዝናብ የቀላቀለው አውሎንፋስ በዋናነት ያጠቃዋል ተብሎ በተገመተው የሰሜን ካሮላይና ግዛት፣የሐገሪቱ ብሔራዊ ጦርን ጨምሮ ድጋፍ የሚያደርጉ አካላት ከዛሬ ረቡዕ ጀምሮ ወደ ስፍራው እየደረሱ መሆናቸውም ታውቋል።
እስረኞችንም ከአደጋው ስፍራ የማረቅ ተግባር ተከናውኗል።25 ያህል የመናፈሻ ስፍራዎችም ተዘግተዋል።