ጠቅላይ ሚንስትር አብይ አህመድ የሚመሩት 33ኛው የኢጋድ የመሪዎች ስብሰባ በአዲስ አበባ እንደሚካሄድ ታወቀ።
( ኢሳት ዜና መስከረም 02 ቀን 2011 ዓ/ም ) ኤርትራ ዳግም ወደ ኢጋድ አባልነት የምትመለስበት ጉዳይ ከስብሰባው አጀንዳዎች አንዱ መሆኑ ታወቀ።
የወቅቱ የኢጋድ ሊቀመንበር ጠቅላይ ሚንስትር አብይ አህመድ የሚመሩት የምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግስታት /ኢጋድ/ 33ኛው የመሪዎች ስብሰባ በመዲናችን አዲስ አበባ የሚካሄድ ሲሆን በሶስት አበይት ጉዳዮች ላይ ይመክራሉ ተብሎ ይጠበቃል።
በእርስ በእርስ ጦርነት የምትታመሰውን ደቡብ ሱዳን ወደ ቀድሞ ሰላሟ መመለስ፣ በቅርቡ ችግራቸውን በሰላም ለመፍታት የተስማማሙት የኤርትራን እና ጅቡቲ ዘላቂ ግንኙነትእንዲሁም ከባልነት ተገላ የቆየችው ኤርትራ ዳግም ወደ ኢጋድ አባልነት የምትመለስበት ሁኔታ ላይ ይመክራሉ።
የኢጋድ የመሪዎች ስብስባ ለመሳተፍ የወቅቱ የአፍሪካ ኅብረት ሊቀመንበር የሆኑት የሩዋንዳው ፕሬዚዳንት ፖል ካጋሜን ጨምሮ የደቡብ ሱዳኑ ፕሬዚዳንት ሳልቫ ኪር እና የሶማሊያው ፕሬዚዳንት መሀመድ አብዱላሂ መሀመድ አዲስ አበባ ገብተዋል።
በድንበር አካባቢዎች እርስ በእርስ በጦርነት ውስጥ የነበሩት የምስራቅ አፍሪካ አገራት ችግራቸውን በሰላማዊ ውይይት እልባት ለመስጠት መሞከራቸው ለቀጠናው መረጋጋት ከፍተኛ አስተዋጾ እያደረገ መምጣቱን የፖለቲካ ተንታኞች ይገልጻሉ።