የኢትዮጵያና የጣሊያን አውሮፕላኖች ለጥቂት ከግጭት ተረፉ

(ኢሳት ዲሲ–መስከረም 1/2011)የኢትዮጵያና የጣሊያን አውሮፕላኖች በኬንያ የአየር ግዛት ውስጥ ለጥቂት ከግጭት መትረፋቸው ተዘገበ።

የኬንያ የአየር ትራፊክ ተቆጣጣሪዎች በኢትዮጵያ የነበረው የአየር ትራፊኮች አድማ ያስከተለው ነው በማለት ተቃውሞ ቢያቀርቡም ክስተቱ ሊያጋጥም የነበረው በኬንያ የአየር ክልል ውስጥ በመሆኑ ውዝግብ ቀስቅሷል።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ አብራሪ ከፍታውን በመጨመር ከጣሊያኑ አውሮፕላን ጋር ባይተላለፍ ኖሮ በአቪየሽን ታሪክ ዘግናኙ አደጋ ይከሰት እንደነበር ዘገባው አመልክቷል።

ዘግይቶ የወጣው ይህ መረጃ እንደሚያመለክተው ከሳምንት በፊት ከጣሊያን ሼሮና ከተማ ወደ ዛንዚባር ሲበር የነበረው የጣሊያኑ ሌይዥር አየር መንገድ አውሮፕላን ከጁሃንስበርግ ወደ ኢትዮጵያ ሲበር ከነበረው የኢትዮጵያ አየር መንገድ አውሮፕላን ጋር በተመሳሳይ የአየር ክልል ውስጥ ሲበሩ የነበሩት በኬንያ የአየር ግዛት ውስጥ እንደሆነም ታውቋል።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ፓይለት በአውሮፕላኑ ላይ በተገጠመው TCAS በተባለ የትራፊክ አደጋ መከላከያ መሳሪያ ችግሩን ከደረሰበት በኋላ ከፍታውን ወደ 38 ሺህ ጫማ በመጨመር ለጣሊያኑ አውሮፕላን የአየር መስመሩን ለቆለታል።

የኢትዮጵያው ፓይለት ይህን በማድረጉ በአቬሽን ታሪክ ዘግናኙ የተባለው አደጋ እንዳይከሰት ሆኗል ብሏል።

እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር ረቡዕ ነሐሴ 29/2018 ልክ ከለሊቱ 6 ሰአት ከ49 ደቂቃ ላይ ከኢትዮጵያ የአየር ክልል ወደ ኬንያ የገባው የጣሊያኑ አየር መንገድ አውሮፕላንና ከታንዛኒያ የአየር ክልል ከባድ የአየር ክልል የተሻገረው የኢትዮጵያ አየር መንገድ አውሮፕላን በተመሳሳይ የአየር ክልል እንዲበሩ የተደረገው በኬንያ አየር ትራፊክ ተቆጣጣሪዎች ስህተት እንደሆነም ተመልክቷል።

ኬንያውያኑ በኢትዮጵያ የነበረውን አድማ በምክንያትነት ቢያቀርቡም ክስተቱ ሊያጋጥም የነበረው ግን በኬንያ የአየር ክልል ውስጥ ስለነበር ኢትዮጵያን ተጠያቂ ማድረጉ በባለሙያዎችም ተተችቷል።

አንድ ከፍተኛ ልምድ ያላቸው የበረራ ባለሙያ አቢያክስ ለተባለው ድረ-ገጽ እንደገለጹት በኬንያ በአየር ክልል ውስጥ ለሚያጋጥም ጉዳይ ተጠያቂዎቹ የኬንያ የአየር ትራፊክ ተቆጣጣሪዎች ናቸው።

ሆኖም ሁሉም አውሮፕላኖች ዘመናዊ የትራፊክ አደጋ መከላከያ ስለተገጠመላቸው አስቀድመው በተመሳሳይ መስመር ላይ ሌላ አውሮፕላን መኖሩን ሊገነዘቡ ስለሚችሉ ርምጃ እንዲወስዱ ያግዛቸዋል።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ፓይለት አደጋውን ለመሸሽ ድንገት ከፍታው ወደ 38 ሺህ ጫማ ሲጨምር በተሳፋሪው ምቾት ላይ መንገጫገጭ ቢፈጥርም ሊከሰት ከነበረው አደጋ ግን ተሳፋሪውን ለመታደግ ሌላ አማራጭ አልነበረውም ብለዋል።