(ኢሳት ዲሲ–ጳጉሜ 2/2010) ኤርትራና ጅቡቲ በመካከላቸው የነበረውን አለመግባባት በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት ስምምነት ላይ መድረሳቸው ተገለጸ።
ሁለቱም ሃገራት ዱሜራ በተባለ ተራራና ደሴት ይገባኛል ጥያቄ ላለፉት 12 አመታት ሲወዛገቡ መቆየታቸው ይታወሳል።
በኢትዮጵያ ሸምጋይነት የተጀመረው ጥረት ተሳክቶ ኤርትራና ጅቡቲ ችግሮቻቸውን በሰላም ለመፍታት ተስማምተዋል።
የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ወርቅነህ ገበየሁ በፌስቡክ ገጻቸው እንዳስታወቁት በኤርትራና ጅቡቲ መካከል የነበረውን አለመግባባት በሰላም ለመፍታት መወሰኑ ታሪካዊ የዲፕሎማሲ ድል ነው።
የጅቡቲው ፕሬዝዳንት ኦማር እስማኤል ጊሌም ሃገራቸው ለእርቅ ዝግጁ ነች ብለዋል።
በኢትዮጵያ ሸምጋይነት የተጀመረው ጥረት ዳር የደረሰው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ወርቅነህ ገበየሁ ከኤርትራና ሶማሊያ አቻቸው ጋር ወደ ጅቡቲ በማምራት ውይይት ካካሄዱ በኋላ መሆኑ ታውቋል።
ኤርትራ ዱሜራ የተባለ ተራራና ደሴት በሃይል ይዛብኛለች የምትለው ጅቡቲ በምን ሁኔታ ጉዳዩን በእርቅ ለመጨረስ እንደተስማማች የተገለጸ ነገር የለም።
በኤርትራና ጅቡቲ መካከል የነበረውን የቦታ ይገባኛል ክርክር ለመሸምገል ኳታር ከዚህ ቀደም ሞክራ ሳይሳካ መቆየቱ ይታወሳል።
ጥረቱ ባለመሳካቱም በሁለቱ አጎራባች ድንበር አካባቢ ኳታር አሰማርታቸው የነበሩ 450 ሰላም አስከባሪ ወታደሮችን እስከማስወጣት ደርሳለች።
በተባበሩት መንግስታት ድርጅት ማዕቀብ የተጣለባት ኤርትራ ከኢትዮጵያና ጅቡቲ ጋር የሰላም ስምምነት ላይ መድረሷ አዎንታዊ ርምጃ መሆኑን የዲፕሎማቲክ ምንጮች ይገልጻሉ።
ኤርትራ ከሶማሊያ ጋር የነበራትንም ውዝግብ በመፍታት ከሃገሪቱ ጋር አዲስ የዲፕሎማሲ ግንኙነት ጀምራለች።
ኤርትራ አልሻባብን ስትረዳ ቆይታለች የሚለውን ውንጀላ ስታስተባብል ነው የቆየችው።
ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አሕመድ ወደ ስልጣን ከመጡና የለውጥ ርምጃ መውሰዳቸውን ተከትሎ በአፍሪካ ቀንድ የተሻለ የሰላም መነቃቃት እየታየ መሆኑን ታዛቢዎች ይናገራሉ።