የአዲስቷ ኢትዮጵያ የጋራ ንቅናቄ ሊቀመንበር አቶ ኦባንግ ሜቶን ጨምሮ 15 አባላት ያለው ቡድን ወደ ኢትዮጵያ ገቡ።
( ኢሳት ዜና ጳግሜን 01 ቀን 2010 ዓ/ም ) የአዲስቷ ኢትዮጵያ የጋራ ንቅናቄ (Solidarity Movement for New Ethiopia) መስራችና ሊቀመንበር የሆኑት የሰብዓዊ መብት ተሟጋቹ አቶ ኦባንግ ሜቶን ጨምሮ 15 አባላትን ያካተተው ቡድን ወደ አገራቸው የገቡ ሲሆን በምንግስት ባለስልጣናት አቀባበል ተደርጎላቸዋል።
ቡድኑ በመንግስት የቀረበለትን የሰላም ጥሪ ተቀብሎ በመላው ኢትዮጵያ በሚደረገው የዴሞክራሲያዊ ሽግግር ሕዝቡ ለሰላማዊ የስልጣን ሽሽግር የነቃ ተሳትፎ እንዲያደርግ የግንዛቤ ማስጨበጥ ዓላማውን ለማስረጽ የበኩሉን ዝግጅት ማጠናቀቁም ታውቋል።
የአዲስቷ ኢትዮጵያ የጋራ ንቅናቄ “ሁላችንም ነጻ ካልወጣን ማንም ነጻ ሊወጣ አይችልም፤ ከጎሳ ይልቅ ለሰብዓዊነት ቅድሚያ እንስጥ!” በሚል መሪ ቃል ፍትህ፣ ሰላምና እኩልነት የሰፈነባት ኢትዮጵያን ለመፍጠር በጋራ በመነጋገር፣ በመደማመጥ፣ በመግባባትና በመተባበር ኢትዮጵያን ለመገንባት የተቋቋመ ግብረሰናይ ድርጅት ነው።
በተለይም ሊቀመንበሩ አቶ ኦባንግ ሜቶ ከአገራቸው ውጪ በስደት ላይ እያሉ የሰብዓዊ መብታቸው ለተጣሱ ኢትዮጵያዊያን ስደተኞች መብት ተቆርቋሪ፤ ጥገኝነትና ከለላ እንዲያገኙ ሲረዱ መቆየታቸው ይታወሳል።