(ኢሳት ዲሲ–ነሐሴ 30/2010) ኢትዮጵያ፣ ኤርትራና ሶማሊያ በአካባቢው ጉዳዮች ላይ የሶስትዮሽ ውይይት ለማድረግ ዛሬ አስመራ ገቡ።
በዚህ ውይይት ላይ ለመሳተፍ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድና የሶማሊያው ፕሬዝዳንት ሙሐመድ አብዱላሒ/ፎርማጆ/ኤርትራ መግበታቸው ተሰምቷል።
ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ በኤርትራ ቆይታቸው ወደ አሰብና ምጽዋ ተጉዘው ሁለቱ ወደቦች አገልግሎት የሚሰጡበትን ሁኔታ መመልከታቸውም ታውቋል።
ካለፈው ቅዳሜ ጀምሮ በቻይና የቆዩት ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አሕመድ ከቤጂንግ ወደ ኤርትራ ያቀኑ ሲሆን ዛሬ ማለዳ አሰብ ሲደርሱ ፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ ተቀብለዋቸዋል።
የአሰብ ወደብን የጎበኙትና በቅርብ ሳምንታት ስራ እንደሚጀምር የተገለጸላቸው ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አሕመድ በምጽዋ የኢትዮጵያ መርከብ ከ20 አመት ወዲህ የመጀመሪያውን ጭነት ይዞ ሲነሳ በስፍራው እንደነበሩም ተመልክቷል።
የኤርትራው ማስታወቂያ ሚኒስትር አቶ የማነ ገብረመስቀል በቲውተር ገጻቸው እንደገለጹት ዛሬ ማለዳ አሰብ የደረሱት ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አሕመድ ቀትር ላይ አስመራ ከሚገቡት የሶማሊያው ፕሬዝዳንት መሐመድ አብዱላሒና ከፕሬዝዳንት ኢሳይስ አፈውርቂ ጋር የሶስትዮሽ ውይይት እንደሚያደርጉ ተመልክቷል።
ስለውይይቱ ግን የተሰጠ ዝርዝር መረጃ የለም።
ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አሕመድ ወደ ስልጣን መምጣታቸውን ተከትሎ የሔጉ የድንበር ኮሚሽን ውሳኔ ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ለመቀበል የተደረሰበት ውሳኔ ስምምነት 20 አመታት የዘለቀውን ውዝግብ ወደ አዲስ አቅጣጫ መርቶታል።
ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አሕመድ በአስመራ እንዲሁም ፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቄ በአዲስ አበባ ያደረጉት ጉብኝት አካባቢውን ወደ ሰላም ቀጠና የቀየረ ጉልህ ርምጃ ተደርጎ በባዕዳን ጭምር ውዳሴን አግኝቷል።
የሶማሊያው ፕሬዝዳንት መሐመድ አብዱላሂ ከወር በፊት ወደ ኤርትራ ያደረጉት ጉዞ እንዲሁም የኤርትራው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ኡስማን ሳላህ ወደ ሞቃዲሾና ከዚያም ወደ አዲስ አበባ የፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂን መልዕክት ይዘው መጓዛቸው የቀውስ ቀጠና በሆነው አካባቢ ሰላማዊ አየር እየነፈሰ ለመሆኑ አመላካች ተደርጎ ተወስዷል።