የራያ ተወላጆች ሰልፍ አካሄዱ

(ኢሳት ዲሲ–ነሐሴ 30/2010) ከወሎ ክፍለ ሃገር ተወስዶ ወደ ትግራይ ክልል ያለፍላጎቱ የተጠቃለለው የራያ ተወላጆች የማንነት ጥያቄ በማንሳት የተቃውሞ ሰልፍ አካሄዱ።

የራያ ተወላጆች በአዲስ አበባ ከተማ ባካሄዱት ሰልፍ በራያ ሕዝብ ላይ የሚፈጸመው የሰብአዊ መብት ረገጣ እንዲቆምና በሕገ መንግስቱ መሰረት ማንነታቸው እንዲከበር ጠይቀዋል።

ሰልፈኞቹ ከኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ቅጥር ግቢ በመነሳት ወደ ፌዴሬሽን ምክር ቤት  አምርተው ጥያቄያቸውን ማቅረባቸው ታውቋል።

የራያ ተወላጆች ያለፍላጎታችን ወደ ትግራይ ተካለናል በሚል ላለፉት ሁለት አስርት አመታት ሲጠይቁ መቆየታቸውን ይናገራሉ።

ጥያቄያቸውን ተከትሎ ግን የትግራይ ክልላዊ መንግስት በራያ ተወላጆች ላይ የሰብአዊ መብት ረገጣ ሲፈጽምባቸው እንደቆየ ገልጸዋል።

የራያ ሕዝብ ስለባህሉ፣ስለታሪኩና ስለማንነቱ ሲጠይቅ ግድያና እስራት ሲፈጸምበት እንደነበር የማንነት ኮሚቴው ሰብሳቢ አቶ አግዘው ሕዳሩ ለኢሳት ተናግረዋል።

በራያ አዘቦ 5 መቶ ወጣቶች በመጠለያ ካምፕ ውስጥ ታጉረው ይገኛሉ ተብሏል።

ብዙ ደግሞ ከአካባቢው ሸሽቶ ተደብቋል።የዚህ ሁሉ ችግር ምክንያት ደግሞ የትግራይ ልዩ ሃይል፣ሚሊሽእዎችና የቀበሌ ታጣቂዎች በሚፈጽሙት ግፍ ምክንያት ነው ይላሉ።

በዚህ የሰብአዊ መብት ረገጣ የተነሳ ታዲያ የአዲስ አበባ የራያ ተወላጆች የማንነት ጥያቄያችን ይከበር በሚል ዛሬ ሰላማዊ ሰልፍ አካሂደዋል።

3 መቶ የሚጠጉ የራያ ተወላጆች ከኢትዮጵያ ቴሌቪዥን በመነሳት ወደ ፌዴሬሽን ምክር ቤት አምርተው ጥያቄያቸውን አቅርበዋል።

በራያ ሕዝብ ላይ ግድያና እስራት የፈጸሙም ለፍርድ ይቅረቡ ሲሉ ነው የጠየቁት።

የራያ የማንነት ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ አገዛው ሕዳሩ እንደሚሉት በትግራይ ክልል ከወሎ ተወስዶ የተጠቃለለው ሕዝብ አማርኛ፣ራይኛና ኦሮምኛ የሚናገር ውሁድ ሕብረተሰብ ነው።

እናም ማንነታችን እንዲከበር፣ በትግራይ ልዩ ሃይል ከሚደርስብን የሰብአዊ መብት ረገጣና በደል እንድንጠበቅ የመከላከያና ፌደራል ፖሊስ ጣልቃ እንዲገቡ እንጠይቃለን ብለዋል።

የራያ የማንነት ኮሚቴ አባላት ጥያቄያቸውን በሰነድ አስደግፈው ለትግራይ ክልላዊ መንግስት ለማቅረብም ዝግጅታቸውን ማጠናቀቃቸውን ለኢሳት ገልጸዋል።

የራያ ሕዝብ ጥያቄ ከወልቃይት የማንነት ጥያቄ ጋር ተመሳሳይነት ያለው ቢሆንም ችግራቸው ግን እስካሁን ጎልቶ ባለመውጣቱ ትኩረት እንዲሰጣቸውና ሕዝቡ እንዲደግፋቸው ጥሪ አቅርበዋል።