(ኢሳት ዲሲ–ነሐሴ 29/2010) የመሰረታዊ ብረታ ብረት ኢንጂነሪንግ ኩባንያ/ሜቴክ/ ለሁለት እንዲከፈል ተወሰነ።
ሜቴክ በወታደራዊና በንግድ ዘርፉ ለሁለት ተከፍሎ ስራውን እንዲያከናውን በተወሰነው መሰረት በመከላከያ ሚኒስቴር ከፍተኛ ባለስልጣናት የተዋቀረ ቡድን ስራውን በማከናወን ላይ መሆኑ ተመልክቷል።
ከፍተኛ ዘረፋ ሲፈጸምበት እንደነበር የሚገለጸው ሜቴክ ዳይሬክተሩ የነበሩትን የህወሃት ጀኔራሉን ክንፈ ዳኘውን ከአራት ወራት በፊት ማሰናበቱ ይታወሳል።
አዲስ ፎርቹን ከአዲስ አበባ እንደዘገበው በጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ትዕዛዝ መሰረት ተቋሙን ለሁለት ለመክፈል የተዋቀረው ቡድን በመከላከያ ከፍተኛ ባለስልጣናት ጄነራል ብርሃኑ ጁላ፣ሌተናል ጀኔራል ሞላ ሃይለማርያምና እና በመከላከያ ሚኒስትሩ አቶ ሞቱማ መቃሳ የሚመራ መሆኑም ተመልክቷል።
ወታደራዊ ነክ ምርቶችን የሚያመርተው የሜቴክ ክፍል በመከላከያ ሚኒስቴር ውስጥ ሲቀጥል አውቶቡስ፣ ትራክተርና ሌሎች መሰል የሲቪል ምርቶችን የሚያመርተው ክፍል በንግድ ዘርፉ እንደሚሰማራም ተመልክቷል።
በጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ከሶስት ሳምንት በፊት የመጨረሻ ውሳኔ ያገኘው ሜቴክን የመክፈሉ ርምጃ በመጪው መስከረም ወር ሙሉ በሙሉ ተጠናቆ ተግባራዊ እንደሚሆንም ተዘግቧል።
ከስምንት ዓመታት በፊት በ10 ቢሊየን ብር ካፒታል የተቋቋመው ሜቴል ከደርግ ግዜ ጀምሮ በሃገሪቱ ውስጥ የነበሩ 15 የሲቪልና የመከላከያ ተቋማትን በማዋሃድ የተቋቋመ ግዙፍ ኩባንያ ነው።
ኩባንያው በሃገሪቱ 10 የስኳር ፕሮጀክቶች እንዲሁም የማዳበሪያና የሃይል ማመንጫዎች ግንባታና አቅርቦት ላይ የተሰማራ ቢሆንም በሁሉም መስክ ውጤታማ ሳይሆን መቅረቱ ሲገለጽ ቆይቷል።
ከፍተኛ የሃገር ሃብት ሲባክንበት መቆየቱም በፓርላማ ጭምር ተጋልጧል።
ሜቴክ የህዉሃት ንብረት ለሆኑት ኤፈርት ኩባንያዎች ኮንትራቶችን በመስጠት በሃገሪቱ ሃብት ህዉሃትን ሲያፋፋ መቆየቱም ሲገለጽ ቆይቷል።
ይህንን ወታደራዊ ተቋም ከምስረታው ጀምሮ ሲመሩ የነበሩት ሜጀር ጀኔራል ክንፈ ዳኘው ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ወደ ስልጣን መምጣታቸውን ተከትሎ መሰናበታቸው ይታወሳል።
በርሳቸው ምትክ የቀድሞው የንግድ ሚኒስትር ዶክተር በቀለ ቡላዶ መሾማቸውም አይዘነጋል።