(ኢሳት ዲሲ–ነሐሴ 22/2010) አቶ በረከት ስምዖንና አቶ ታደሰ ካሳ ከብአዴን ማዕከላዊ ኮሚቴ አባልነት የታገዱት በጥረት ድርጅት ውስጥ በተፈጸመ የገንዘብ ዘረፋና ብክነት ጋር በተያያዘ መሆኑን ብአዴን ገለጸ።
የብሄረ አማራ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ ብአዴን የማዕከላዊ ኮሚቴ ጽ/ቤት ሃላፊ አቶ ምግባሩ ከበደ በተለይ ለኢሳት እንደገለጹት አቶ በረከት ስምዖን በተለያዩ ሚዲያዎች ብአዴንን በተመለከተ የሚያቀርቡት ውንጀላ መስረተ ቢስ ነው ብለዋል።
ብአዴን የፖለቲካ ውሳኔ መስጠቱን የገለጹት አቶ ምግባሩ ተፈጸመ የተባለውን ዝርፊያ በማስረጃ የተደገፈ ወንጀልን በተመለከተ ይህግ አካል የሚያየው ጉዳይ ነው ሲሉ ገልጸዋል።
በተያያዘ ዜና ለብአዴን ግልጽ ደብዳቤ የጻፉት አቶ በረከት ስምዖንና አቶ ታደሰ ካሳ የብአዴን ማዕከላዊ ኮሚቴ አባላት የበቀል እርምጃ ወስደውብናል ብለዋል።
አቶ በረከት ስምዖን ሰሞኑን መገናኛ ብዙሃን ላይ በርክተዋል። በሀገር ውስጥና በውጭ ሀገራት በአማርኛ ቋንቋ በሚሰራጩ የራዲዮ ጣቢያዎች አቶ በረከት እየተናገሩ ነው።
ባለፈው ዓርብ የብ አዴን ማዕከላዊ ኮሚቴ በሁለት አባላቱ ላይ የእገዳ ውሳኔ ማስተላለፉን ተከትሎ ድምጻቸውን ማሰማት የጀመሩት አቶ በረከት ስምዖን የብአዴን አመራሮች ላይ መጠነ ሰፊ ዘመቻ ጀምረዋል።
አብረዋቸው ከታገዱት ከአቶ ታደሰ ካሳ ጋር በመሆን ለብአዴን በጻፉት ደብዳቤ ላይም ክስና ተቃውሞ በማቅረብ የተላልፈባቸውን ውሳኔ ህገወጥ ነው ብለዋል። የአሁኖቹ የብ አዴን
አመራሮች እኛን ለማገድ ምንም ምክንያት የላቸው ያሉት አቶ በረከት የተበላሹና ለሀገር ጠንቅ የሆኑ አመራሮች ናቸው ሲሉ ተናግረዋል።
የብሄረ አማራ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ ብ አዴን ለአቶ በረከት ስምዖን ክስና ውንጀላዎች መላሽ ሰጥቷል።
ኢሳት ያነጋገራቸው የብአዴን ማዕከላዊ ኮሚቴ ጽ/ቤት ሃላፊ አቶ ምግባሩ ከበደ አቶ በረከት እንዲህ ዓይነት በነጻነት የመናገር መብት የሰጣቸው አሁን ያለው አመራር ዲሞክራሲያዊ በመሆኑ ሲሉ ገልጸዋል።
አቶ በረከት በእሳቸው ዘመን ብዙዎቹን አባላት ሲያግዱ ኖረው በእሳቸው ላይ ተገቢ እርምጃ ሲወሰድ ችግር የሚሆነው ለምንድን ነው ሲሉም ጠይቀዋል አቶ ምግባሩ። የአቶ በረከት ክስ መሰረተ ቢስ ነውም ብለዋል።
ብአዴን በሁለቱ ነባር አመራሮቹ ላይ እርምጃ የወሰደው ጥረት ከተሰኘው ድርጅት ጋር በተያያዘ በተፈጸመ የገንዘብ ዘረፋና ብክነት መሆኑን የገለጹት አቶ ምግባሩ ከበደ በተጨባጭ ማስረጃ በታገዘ እርምጃው ተወስዶባቸዋል ሲሉም ገልጸዋል።
የብአዴን ማዕከላዊ ኮሚቴ ጽ/ቤት ሃላፊ አቶ ምግባሩ ከበደ ብ አዴን ፖለቲካዊ ውሳኔ ማስተላለፉን ጠቅሰው የህግ ጉዳይን የሚመለከተው አካል ሃላፊነት እንደሚሆን ገልጸዋል።