በምስራቅ ኦሮምያ አካባቢ በሶማሊ ልዩ ሃይል አባላትና በኦሮምያ ፖሊስ መካከል የተኩስ ልውውጥ ተካሄደ

በምስራቅ ኦሮምያ አካባቢ በሶማሊ ልዩ ሃይል አባላትና በኦሮምያ ፖሊስ መካከል የተኩስ ልውውጥ ተካሄደ
( ኢሳት ዜና ነሐሴ 22 ቀን 2010 ዓ/ም ) በምስራቅ ኦሮምያ ባቢሌ ወረዳ የሶማሊ ልዩ ሃይል አባላት ወደ ገጠር በመግባት በህዝቡ ላይ ጥቃት በመክፈት ጉዳት ማድረሳቸውን የአካባቢው ነዋሪዎች ተናግረዋል። የኦሮምያ ፖሊስ በወሰደው የመከላከል እርምጃ 7 ወታደሮች መገደላቸውን የአካባቢው ነዋሪዎች ተናግረዋል። የልዩ ሃይል አባላቱ 2 የኦሮምያ ፖሊሶችን መምታታቸው ታውቋል። የመከላከያ ሰራዊት በሶማሊ ልዩ ሃይል አባላት ላይ ጥቃት በመሰንዘር ከአካባቢው እንዲርቁ እንዳደረጋቸውና በአሁኑ ሰዓት አካባቢው መረጋጋቱን ነዋሪዎች ተናግረዋል።
ትጥቃቸውን ያልፈቱ የአብዲ ኢሌ ወታደሮች ወደ ገጠሮች አካባቢ በመሰማራት የአካባቢውን ሰላም እያወኩት ነው። ምንም እንኳ በጅግጅጋና አካባቢው አንጻራዊ ሰላም ቢሰፍንም፣ ከኦሮምያ ጋር በሚዋሱ የገጠር ቀበሌሎች አልፎ አልፎ ግጭቶች እየተከሰቱ ነው።
አዲሱ የሶማሊ ክልል አስተዳደር አብዲ ኢሌ ሲመራቸው በነበሩ የልዩ ሃይል አባላት ላይ የሚወስደው እርምጃ አልታወቀም። ይሁን እንጅ መስተዳድሩ በወንጀል የሚጠየቁ የቀድሞ ባለስልጣኖችንና የልዩ ሃይል አዛዦችን ለፍርድ ለማቅረብ የአንዳንዶች ያለመከሰስ መብት እንዲነሳ አድርጓል። አዲሱ የክልሉ ፕሬዚዳንት አቶ ሙስጠፋ ኡመር በወንጀል የተሳተፉት ሁሉ ለፍርድ እንደሚቀርቡ ተናግረዋል።
የክልሉ ፕሬዚዳንት አቶ አብዲ ሙሃመድ ኡመር ሰኞ እለት አዲስ አበባ ከሚገኘው መኖሪያ ቤታቸው ተይዘው ታስረዋል። አቶ አብዲ ክልሉን ሲመሩ በነበረበት ወቅት በፈጸሙዋቸው ወንጀሎች ክስ ይቀርብባቸዋል።