አቃቢ ህግ በሰኔ 16 የመስቀል አደባባይ ፍንዳታ ክስ መመስረት አለመቻሉ ተዘገበ
( ኢሳት ዜና ነሐሴ 16 ቀን 2010 ዓ/ም ) የፌዴራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ቢሮ መርማሪ ቡድን በሰኔ 16 ቀን 2010 ዓ.ም. በመስቀል አደባባይ በደረሰው የቦምብ ፍንዳታ ተጠርጣሪዎች ላይ ምርመራውን አጠናቆ ለዓቃቤ ሕግ ቢያስረክብም፣ ዓቃቤ ሕጉ ክስ ከመመስረት ለድጋሚ ምርመራ ለመርማሪ ቡድኑ መዝገቡን መመለሱን ለፍርድ ቤት ማስታወቁን ሪፖርተር ዘግቧል።
አቃቢ ህግ የምርመራ መዝገቡን የመለሰበት ምክንያት በቦምብ ፍንዳታው ጉዳትየደረሰባቸው ከ100 በላይ ቢሆንም፣ መርማሪው ፖሊስ ግን የ40 ሰዎችን ቃል ብቻ የተቀበለ በመሆኑ ነው።
ቦምብ በማቀበል የተጠረጠረው አቶ ብርሃኑ ጃፋርና ቦምቡን ወርውሮ ሊያመልጥ ሲል ተይዟል የተባለው ተጠርጣሪ ጥላሁን ጌታቸው፣ ከሰኔ 12 እስከ 16 ቀን 2010 ዓ.ም. ያደረጉትን የስልክ ንግግር ከኢትዮ ቴሌኮም አስወጥቶ የምርመራ መዝገቡ አካል ማድረግ ስለሚቀረው አጠናቆ እንዲያስረከበው ለመርማሪ ቡድኑ መዝገቡን መመለሱን ለፌዴራል የመጀመርያ ደረጃ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ ተረኛ ችሎት ተናግሯል።
መርማሪ ቡድኑም በ7 ቀናት ውስጥ ምርመራው አጠናቆ ለማስረከብ በጠየቀው ቀጠሮ መሰረት ምርመራውን ጨርሶ ለነሃሴ 21 ቀን 2010 ዓም ቀጠሮ ተሰጥቷል።
በሌላ በኩል በከባድ የሙስና ወንጀል ተጠርጥረው በእስር ላይ በሚገኙት የቀድሞ የመረጃ መረብ ደኅንነት ኤጀንሲ (ኢንሳ) ምክትል ዋና ዳይሬክተር ላይ፣ ክስ እንዲያቀርብና ውጤቱንም እንዲገልጽ ፍርድ ቤት ትዕዛዝ ሰጥቷል።
የፌዴራል ፖሊስ መርማሪ ቡድን በተጠርጣሪ አቶ ቢኒያም ተወልደና አቶ ሰላም ይሁን አደፍርስ ላይ የጀመረውን ምርመራ አጠናቆ፣ ለዓቃቤ ሕግ እንዲያስረክብ ተሰጥቶ የነበረውን የፍርድ ቤት ትዕዛዝ ሳይፈጽም ቀርቷል።
ፍርድ ቤቱም በተከሳ ጠበቆች የቀረበውን የዋስትና ጥያቄ ባለመቀበል አቃቢ ህግ ክስ እንዲመሰርት ትዕዛዝ ሰጥቷል።