የዚምባቡዌ ህገ መንግስታዊ ፍርድ ቤት በምርጫው ውጤት ላይ ዋነኛው ተቃዋሚ ፓርቲ ያቀረበውን ክስ አዳመጠ።

የዚምባቡዌ ህገ መንግስታዊ ፍርድ ቤት በምርጫው ውጤት ላይ ዋነኛው ተቃዋሚ ፓርቲ ያቀረበውን ክስ አዳመጠ።
( ኢሳት ዜና ነሐሴ 16 ቀን 2010 ዓ/ም ) የዲሞክራሲ ለውጥ ንቅናቄ ትብብር ወይም በምህጻረ ቃሉ- ኤም፣ዲ ሲ ፕሬዚዳንት ምናንጋግዋን አሸናፊ ያደረገውን የምርጫ ውጤት በመቃወም ነው ክስ ያቀረበው።
ምናንጋዋ ምርጫውን ያሸነፉት በ 30 ሺህ የድምጽ ብልጫ እንደሆነ ነው በምርጫ ኮሚሽኑ የተገለጸው።
የተቃዋሚ ፓርቲው አመራሮች ግን ፣ ሮበርት ሙጋቤ ከስልጣን ከተወገዱ በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ባለፈው ግንቦት ወር የተካሄደው ይህ ምርጫ በገዥው ዛኑ ፓርቲ ተጭበርብሯል ባይ ናቸው።
የሀገሪቱ የምርጫ ኮሚሽን ደግሞ በምርጫውም ሆነ በድምጽ ቆጠራው ወቅት ምንም አይነት የማጭበርበር ድርጊት እንዳልተፈጸመ ይገልጻል።
ፕሬዚዳንት ምናንጋግዋ በበኩላቸው የሹመት ስነ ስር ዓታቸው ተካሂዶ ሥልጣን ከተረከቡና ሥራቸውን ከጀመሩ በኋላ በተቃዋሚ ትብብር ፓርቲው የቀረበውን አቤቱታ ውድቅ እንዲያደርገው በፍርድ ቤቱ ላይ ግፊት እያደረጉ ነው።
ሕገ መንግስታዊው ፍርድ ቤት በጉዳዩ ዙሪያ ከነገ በስቲያ አርብ ውሳኔ እንደሚሰጥ አሳውቋል። የተቃዋሚው መሪ ኔልሰን ቻሚሳ በትዊተር ገጻቸው ለደጋፊዎቻቸው ባስተላለፉት መልዕክት፦የህግ ቡድናቸው የሕዝብን ድምጽ ለማስከበር ዝግጁ መሆኑን አስታውቀዋል።