የኢትዮጵያ የእስልምና አባቶች እስልምና የሰላምና የአንድነት ምንጭ መሆኑን ሰበኩ
( ኢሳት ዜና ነሐሴ 15 ቀን 2010 ዓ/ም ) ዛሬ በአዲስ አበባ ተከብሮ በዋለው 1ሺ 439ኛው የኢድ አል አድሃ ( አረፋ) በአል ላይ የተገኙት የሃይማኖቱ አባቶች እስልምና የሰላምና አንድነት መሰረት መሆኑን ተናግረዋል። ሙስሊሙ ማህበረሰብ ሰላምን በመጠበቅ፣ የአገሩን አንድነት በመጠበቅ አገሩን ማሳደግ እንዳለበት የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ተወካይ ተቀዳሚ ሙፍቲ ሀጂ ዑመር እድሪስ ተናግረዋል።
ሃጂ ኡመር እስልምና ማለት ሰላም ነው፣ የሰላም መፍለቂያ ነው፣ የአንድነት መፍለቂያ ነው፣ የመተባበር፣ የመከባበር መፍለቂያ ነው ብለዋል።
ሃጂ ኡመር አክለውም እያንዳንዱ ለራሱ የሚያስደስተውን ለሌላው ወንድሙ ካልተመኘ ትክክል አይደለም ያሉ ሲሆን፣ በራሳችን እንዲሆን የማንፈልገውን በሌሎች ላይ እንዲደርስ ማድረግ ከእስልምና አስተምሮት ውጭ ነው።
ሃጂ ኡመር ሙስሊሙ ማህበረሰብ አርቆ ማየት እንዳለበት ወደ አንድነት ወደ ሰላምና ልማት መመለስ እንደሚገባው ሃይማኖታዊ፣ አባታዊና አገራዊ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።
ኡስታዝ አቡበክር አህመድም እንዲሁ እስልምና ሰላም መሆኑን ጥቅሰው በየትም መልኩ የሰው ህይወት እንዳይጠፋ፣ ሁከት እንዳይነሳ መመሪያ ያስተላለፈ ሃይማኖት በመሆኑ፣ በእኛ እጅ አደጋ ሊደርስ ለጥፋት ምክንያት ልንሆን አንችልም ብለዋል።
በሌላ በኩል ደግሞ በጎንደር ከተማ የሚገኙ ሙስሊሞች በተለያዩ አካባቢዎች የደረሱ የእምነት ተቋማት ቃጠሎዎችን የሚያወግዝዙ መፈክሮችን ይዘው ወደ አደባባይ ወጥተዋል።
የደሴ ሙስሊሞችም እንዲሁ በእምነት ተቋማት ላይ የሚደርሰውን ጥቃት አውግዘው፣ የመቅበሪያና የመስገጃ ቦታዎችን አጥተው የተቸገሩ የአክሱም ሙስሊሞችም ፍትህ እንዲሰጣቸው ጠይቀዋል።