በሰሞኑ የጅግጅጋ ግጭት በአብዲ ኢሌይ ኃይላት የተከፈተባቸውን ጥቃት በመሸሽ ሀረር ከተማ ውስጥ ተጠልለው የነበሩ በመቶ የሚቆጠሩ ተፈናቃዮች ወደ ጅግጅጋ ተመለሱ።
( ኢሳት ዜና ነሐሴ 15 ቀን 2010 ዓ/ም ) የኢሳት ወኪል ከሥፍራው እንደዘገበው ፣ተፈናቃዮቹ ወደ ጅግጅጋ እንዲመለሱ የተደረገው ከተማው በመረጋጋቱና የአካባቢው ሰላም ወደ ቀድሞው ሁኔታ በመመለሱ ነው።
በአብዲ ኢሌይ ሲመሩ የቆዩት የልዩ ኃይል አባላት በፈጸሙት ጥቃት ከአርባ በላይ ሰዎች መገደላቸውና አስራ አንድ አብያተ ክርስቲያናት መቃጠላቸው ይታወቃል።
ይሁንና የተፈጸመውን ድርጊት በጥብቅ ከማውገዝ ጀምሮ ተፈናቃዮችን ዳግም እስከ ማቋቋም ድረስ በተደረገው ጥረ ኢትዮጵያውያን ሀይማኖትና ዘር ሳይለያቸው ከዳር እስከ ዳር በአንድነት መቆማቸው ብዙዎችን አስደስቷል።
በዚህ ሂደት ተሳታፊ ከሆኑት መካከል የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ምክር ቤትን ጨምሮ ሁሉም የእምነት ተቋማት፣ የጅግጅጋን ጨምሮ የተለያዩ ከተሞች ነዋሪዎች ይገኙበታል።
በአሁኑ ወቅትም የተለያዩ ከተሞች ነዋሪዎች እና የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ተፈናቃዮቹን እስከመጨረሻው ለመርዳት ርብርብ ማድረጋቸውን ቀጥለዋል።