በኢትዮጵያ እና ኤርትራ እርቅ ዙሪያ የአርበኞች ግንቦት ሰባት አመራሮች ሚና ጉልህ ድርሻ እንደነበረው የንቅናቄው ዋና ጸሀፊ ታጋይ አንዳርጋቸው ጽጌ ገለጹ።
( ኢሳት ዜና ነሐሴ 14 ቀን 2010 ዓ/ም ) አቶ አንዳርጋቸው ይህን የገለሱት በዋሽንግተን ዲሲ በተደረገ ታላቅ ስብሰባ ላይ የኤርትራ መንግስት የነጻነት ትግሉን በማገዝ በኩል ላደረገው ድጋፍና ውለታ ምስጋና ባቀረቡበት ጊዜ ነው።
አንዳንድ ወገኖች ኤርትራና ኢትዮጵያ ከ20 ዓመታት በኋላ ወደ እርቅ የመጡት በውጭ ኃይሎች ተጽዕኖ እንደሆነ መላምት ሢሰነዝሩ ቢደመጡም፤ አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ ግን ሀገራቱ ወደ እርቅና ፍቅር የመጡት ያለ አንድም የውጭ ኃይላት ሸምጋይ እንደሆነ አስረግጠው ተናግረዋል።
ይልቁንም የአርበኞች ግንቦት ሰባት ንቅናቄ በዚህ ረገድ ገንቢ ሚና መጫዎቱን የጠቀሱት አቶ አንዳርጋቸው፣”ንቅናቄያችን በወቅቱ የኢትዮጵያ መንግስትም ሆነ በኤርትራ መንግስት አመኔታን ያተረፈ ነው” ብለዋል።
በርካታ የንቅናቄው ደጋፊዎች በታደሙበት በዲሲው ስብሰባ ታጋይ አንዳርጋቸው የተለያዩ ሽልማቶች የተበረከቱላቸው ሲሆን፣ ዝግጅቱ ላይ ለጨረታ የቀረበውን የገዛኸኝ ነብሮብን ምስል የባልቲሞር ወጣቶች አሸንፈዋል።
አቶ አንዳርጋቸው ቀደም ሲል በሌላ ከተማ በተሰናዳ ተመሣሳይ መድረክ በእስር ቤት ሳሉ የተወሰዱባቸውን የመጽሀፍ ረቂቅ ሶፍት ኮፒ ዶክተር አብይ አሕመድ እንደላኩላቸው፣ በየመን ሰንዓ ሲታገቱ የተወሰደውንም 4 ሺህ ዶላር እንደመለሱላቸው በማውሳት፤ ለጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አሕመድ የተለዬ ክብርና አድናቆት እንዳላቸው መግለጻቸው ይታወሳል። ይህ በእንዲህ እንዳለ የአርበኞች ግንቦት ሰባትን ቅናቄ በትናንትናው ዕለት በአዲስ አበባ ኢየሩሳሌም ሆቴል የተሳካስብሰባ አድርጓል።
የፋኖ፣ የቄሮ እና የዘርማ ተወካዮችን ጨምሮ ከየክፍለ ከተማው የተውጣጡ በርካታ ወጣቶች በተገኙበት በዚህ ስብሰባ ላይ በቅርቡ ወደ ሀገር ቤት የሚገቡትን የንቅናቄውን አመራሮች በልዩ ድምቀት መቀበል በሚቻልበት ሁኔታ እና በሌሎች ወቅታዊ ጉዳዮች ሰፊ ውይይት መካሄዱ ታውቋል።