በኦሮሞ ነጻነት ግንባር-ኦነግ ስም የሚደረጉ ህገ ወጥ ድርጊቶች ድርጅቱን እንደማይወክል የኦነግ ቃል አቀባይ ገለጹ።

በኦሮሞ ነጻነት ግንባር-ኦነግ ስም የሚደረጉ ህገ ወጥ ድርጊቶች ድርጅቱን እንደማይወክል የኦነግ ቃል አቀባይ ገለጹ።
( ኢሳት ዜና ነሐሴ 14 ቀን 2010 ዓ/ም ) ቃል አቀባዩ አቶ ቶሌራ አደባ ኦነግ ሰላም ለማወክ እንደማይንቀሳቀስ በመጥቀስ፤ በክልሉ አንዳንድ ቦታዎች የሚታዩ ህገወጥ ድርጊቶች ግንባሩን እንደማይወክሉ አረጋግጠዋል።
“ኦነግ የኦሮሞን ህዝብ ሰላም እና ደህንነት ለማደፍረስ ሳይሆን ህዝቡን ከስጋት እና ሮሮ በማውጣት” ነው የሚሠራው ያሉት ቃል አቀባዩ፤ ግንባሩ ዓላማውም ለህዝቡ የሚመኝለትን ሰላም እና ዴሞክራሲማጎናጸፍ እንደሆነ አስረድተዋል።
ከቀናት በፊት የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ለማ መገርሳ በክልሉ እየተስተዋሉ ያሉ ህገ ወጥ ድርጊቶች ኦነግን እንደማይወክሉ ከግንባሩ አመራሮች ጋር ባደረጉት ውይይጥ ማረጋገጣቸውን በመጥቀስ፦”በኦሮሞ ስም መደራጀት ይቻላል። ሰላምን ማደፍረስ ግን አይቻልም። መንግስት ሰላም የማስከበር ኃላፊነት አለበት”ማለታቸው ይታወሳል።
ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ በበኩላቸው ትናንት በሰጡት መግለጫ መንግስታቸው በተያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች እያቆጠቆጡ ያሉ ህገ ወጥነቶችን እና የጎዳላና ላይ ፍርዶችን እንደማይታገስ አስጠንቅቀዋል።
“ስለ ፍቅር እና ይቅርታ ስንል እንደመር ማለት መረን እንውጣ፣ ህግ አይከበር፣ ሥርዓት አልበኝነት ይንገስ ማለታችን አይደለም”ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ።