(ኢሳት ዲሲ–ነሐሴ 11 / 2010) በህገወጥ መንገድ የገቡ ከአንድ ሺህ በላይ ሽጉጦችና መሰል ጥይቶች መያዛቸውን ፖሊስ አስታወቀ።
መነሻው ካልተገለጸ አካባቢ በነዳጅ ቦቲ ተሽከርካሪ ተጭነው በአዲስ አበባ የተያዙት አንድ ሺህ ሃምሳ አንድ ሽጉጦችና አራት ሺህ ሰላሳ ጥይቶች መሆናቸውን የፌደራል ፖሊስ ገልጿል።
ከጉዳዩ ጋር በተያያዘ ሶስት ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር መዋላቸውም ታውቋል።
በሌላ በኩል በህገወጥ መንገድ ሲዘዋወሩ የነበሩ የውጭ ሀገር ገንዞቦችን መያዙን መንግስት አስታውቋል።
በቦሌ አውሮፕላን ማረፊያ የተያዙት የውጭ ሀገር ገንዘቦች ከ92ሺህ በላይ የአሜሪካን ዶላርና ሌሎች ገንዘቦች እንደሆኑም ተገልጿል።
ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ስልጣን ከጨበጡ ወዲህ ህገወጥ የመሳሪያና የገንዘብ ዝውውር ተበራክቷል።
ባለፉት ሳምንታት በተለያዩ የሃገሪቱ አካባቢዎች የመሳሪያና የገንዘብ ዝውውሩ በከፍተኛ መጠን ሲካሄድ እንደነበር መገለጹ የሚታወስ ነው።
በፖሊስ ቁጥጥር ስር የዋሉትን ዝውውሮች መነሻ በማድረግ ከእይታ ውጭ በሀገሪቱ ውስጥ የተስፋፋ የህገወጥ መሳሪያና ገንዘብ ሊኖር እንደሚችል ግምቶች አሉ።
ገንዘቡና መሳሪያው የህዝብን ሰላም ለማደፍረስና የተጀመረውን የለውጥ ሂደት ለመቀልበስ የተላኩ እንደሚሆኑም ይነገራል። ምንጫቸው ከየት እንደሆነ ግን እስካሁን የታወቀ ነገር የለም።
የፌደራል ፖሊስ የወንጀል ምርመራ ቢሮ ዛሬ እንዳስታወቀውም በህገ-ወጥ መንገድ ወደ አዲስ አበባ የገቡ 1 ሺህ 51 ሽጉጦችና በርካታ ጥይቶች በቁጥጥር ሥር ውለዋል።
በህብረተሰቡ ጥቆማ የጦር መሳሪያዎቹ በነዳጅ መጫኛ ቦቴ እና አይሱዙ የጭነት ተሽከርካሪዎች ውስጥ እንዳሉ በቁጥጥር ስር መዋላቸውን ነው ፌደራል ፖሊስ ያስታወቀው።
4038 የሽጉጥና ክላሽ ጥይቶችን ደግሞ በአይሱዚ የጭነት መኪና ሊገባ ሲል ተይዟል ብሏል ፖሊስ።
በአዲስ አበባ ኮልፌ አካባቢ የተያዙት እነዚህ መሳሪያና ጥይት የጫኑ ተሽከርካሪዎች መነሻቸው ከየት እንደሆነ አልተገለጸም።
ከጉዳዩ ጋር በተያያዘ ሶስት ሰዎች በቁጥጥር ስር ውለው ምርመራ እየተደረገባቸው እንደሆነም የፌደራል ፖሊስ የወንጀል ምርመራ ቢሮ አስታውቋል።
በሌላ በኩል በሕገወጥ መንገድ ሲዘዋወሩ የነበሩ የውጭ ሃገር ገንዘቦች በቁጥጥር ሥር ማዋላቸውን የገቢዎችና ጉምሩክ ባለስልጣን ገልጿል።
ከ92 ሺህ በላይ የአሜሪካ ዶላርና ሌሎችም የተለያዩ የውጭ ሃገር ገንዘቦች በሕገወጥ መንገድ ሲዘዋወሩ ቦሌ አውሮፕላን ማረፊያ በቁጥጥር ሥር መዋላቸውን ነው ባለስልጣኑ ያስታወቀው።