ኢሳያስ አፈወርቂ በአማራ ክልል ጉብኝት ሊያደርጉ ነው

(ኢሳት ዲሲ–ነሐሴ 11/2010)የኤርትራው ፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ በአማራ ክልል ጉብኝት እንደሚያደርጉ ተገለጸ።

በፕሬዝዳንቱ የሚመራው የልኡካን ቡድን ወደ አማራ ክልል እንደሚመጣ የአማራ ክልል መንግስት ኮሚኒኬሽን ሃላፊ አቶ ንጉሱ ጥላሁን ናቸው።

በአስመራ ቆይታ ያደረገው የአማራ ክልል የልኡካን ቡድን ከአማራ ዴሞክራሲያዊ ሃይል ንቅናቄ አመራሮች ጋር መወያቱ ታውቋል።

ፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ በአማራ ክልል የሚያደርጉት ጉብኝት መቼና በምን ጉዳዮች ላይ የሚያተኩር እንደሚሆን ግን በዝርዝር አልተገለጸም።

በሌላ በኩል የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከ41 አመት በኋላ ወደ ሞቃዲሾ በረራ ሊጀምር ነው ተብሏል።

የአማራ ክልል ኮሚኒኬሽን ጽሕፈት ቤት ሃላፊ አቶ ንጉሱ ጥላሁን እንደገለጹት ፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ ወደ አማራ ክልል በመምጣት ጉብኝት እንዲያደርጉ ከስምምነት ላይ ተደርሷል።

የሕዝባዊ ግንባር ለዴሞክራሲና ፍትህ የፖለቲካ ዘርፍ ሃላፊ እና የፕሬዝዳንት ኢሳያስ ልዩ አማካሪ ከሆኑት ከአቶ የማነ ገብረአብ ጋር ውይይት መደረጉን የጠቀሱት አቶ ንጉሱ ጥላሁን በአቶ ኢሳያስ አፈወርቂ የሚመራ የልዑካን ቡድን ወደ አማራ ክልል እንዲመጣ መስማማታቸውን ገልጸዋል።

ጉብኝቱ መቼና በምን ጉዳይ ላይ እንደሚያተኩር ግን ዝርዝር መረጃ ከመስጠት ተቆጥበዋል።

አቶ ኢሳያስ በኢትዮጵያና ኤርትራ መካከል ለ20 ዓመታት ተቋርጦ የነበረው ግንኙነት በአዲስ መልክ ከተጀመረ ወዲህ ኢትዮጵያን ሲጎበኙ የአማራ ክልሉ ለሁለተኛ ጊዜ ሆኖ ይመዘገባል።

የአማራ ክልል ልዩ የልዑካን ቡድንም ወደ ኤርትራ በቅርቡ እንደሚያመራ አቶ ንጉሱ ጥላሁን ገልጸዋል።

አቶ ንጉሱ ሰሞኑን የክልላቸውን መንግስት ወክለው አንድ የልዑካን ቡድን በመምራት አስመራ ቆይታ ማድረጋቸው መዘገቡ ይታወሳል።

በዚህን ወቅት በኤርትራ ብረት አንስቶ እየታገለ ከሚገኘው የአማራ ዴሞክራሲያዊ ሃይል ንቅናቄ ጋር መወያያቱ ተገልጿል።

ንቅናቄው ወደ ሀገር ቤት በመግባት በሰላማዊ መንገድ ትግሉ እንዲቀጥል ከስምምነት ላይ መደረሱንም አቶ ንጉሱ ጥላሁን አስታውቀዋል።

በኤርትራ ቆይታ ወቅት ከሀገሪቱ ከፍተኛ ባለስልጣናት ጋር ምክክር መደረጉን የጠቀሱት አቶ ንጉሱ ጥላሁን በኢትዮጵያና በኤርትራ መካከል የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነት ማጠናከር በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ውይይት መደረጉም ተመልክቷል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ ሶማሊያ በረራ ሊጀመር መሆኑ ተገልጿል።

ወደ ሞቃዲሾ የሚደረገው በረራ ከ41 ዓመታት በኋላ መሆኑ የተገለጸ ሲሆን በሳምንት ሶስት ጊዜ እንደሚደረግም ለማወቅ ተችሏል።

ከሶማሊያ ወደ አዲስ አበባ ለመምጣት በጅቡቲና በናይሮቢ ሲደረግ የነበረውን በረራ የሚያስቀረው የሞቃዲሾው አዲሱ መስመር መቼ እንደሚጀመር ግን የተገለጸ ነገር የለም።