(ኢሳት ዲሲ–ነሐሴ 11 / 2010) በ27 አመታት የተሰሩ ሥራዎችን እየደመሰሱ ለውጥ አመጣለሁ ማለት አይቻልም ሲሉ የሕወሃት ሊቀመንበር ዶክተር ደብረጽዮን ገብረሚካኤል ገለጹ።
ሕገ መንግስቱ ይከበር ማለትም ለውጡን ማደናቀፍ ሊሆን አይችልም ሲሉም አክለዋል።
በቅርቡ በመቀሌ የተካሄደው ሰልፍ የትግራይ ሕዝብ አንድነት የታየበት መሆኑን የገለጹት ዶክተር ደብረጽዮን ገብረሚካኤል ይህ አንድነት ከፖለቲካ ፓርቲዎች፣ ከአረናም ጋር ጭምር አንድነት የተንጸባረቀበት እንደሆነም አመልክተዋል።
ሰልፉ ሕገመንግስቱ እንዲከበር ለመጠየቅ እንዲሁም በትግራይ ተወላጆች እና በሌሎች ላይ በየቦታው የሚካሄደው ግድያ እንዲቆም ለማሳሰብ መሆኑን የገለጹት የትግራይ ክልል ምክትል ፕሬዝዳንት ዶክተር ደብረጽዮን ገብረሚካኤል ከኤርትራ ጋር የተደረገውን ስምምነት ለመደገፍ እና ይህም ሕዝብ እንዲመክርበት ጭምር ሰልፉ መዘጋጀቱን ገልጸዋል።
የኢንጂነር ስመኘው በቀለን ግድያ ማውገዝም የሰልፉ አካል መሆኑን የገለጹት የትግራይ ክልልምክትል ፕሬዝዳንት ዶክተር ደብረጽዮን ገብረሚካኤል በሌላ አካባቢ የትግራይ ተወላጆች ሲገደሉ እዚህ ሌሎች የማይገደሉት ሌሎች ብሔሮች ስለሌሉ አይደለም ፣ርምጃው ሰለማይጠቅም እና መበታተን ሰለሚያስከትል እንጂ ብለዋል።
በ27 ዓመታት የተሰሩ ሥራዎችን እየደመሰሱ ለውጥ አመጣለሁ ማለት አይቻልም ያሉት የትግራይ ክልል ምክትል ፕሬዝዳንት እና የሕወሃት ሊቀመንበር ዶክተር ደብረጽዮን ገብረ ሚካኤል በዓለም ላይ በፈጣን ዕድገቷ የተመሰከረላትን መካድ እንደማይቻልም አመልክተዋል።
ዶክተር ደብረጽዮን ገብረሚካኤል ከመገናኛ ብዙሃን ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ እንበታተናለን የሚለውን ቃል ደጋግመው የተጠቀሙ ሲሆን እንከባበር የሚል መልዕክትም አስተላልፈዋል።
ሕገ-መንግስቱ ካልተከበረ የመበታተን አደጋ እንደሚገጥም በሰላማዊ ሰልፍ ከገለጽን በኋላ በሳምንታት ውስጥ በሶማሌ ክልል የገጠመው አደጋ የሥጋታችን ማሳያ ነው በማለት በአስረጂነት ጠቅሰዋል።
በሶማሊያ ክልል አደጋው ከተከሰተ በኋላ ፌደራል መንግስቱ ቀውሱን ለመግታት ሲንቀሳቀስ የተቃውሞ መግለጫ ስላወጡበት ምክንያት ግን ማብራሪያ ከመስጠት ተቆጥበዋል።