የብሄረ አማራ ዲሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ብአዴን) ከወረዳ ጀምሮ በርካታ አመራሮቹን እያነሳ መሆኑን ተከትሎ በክልሉ አለመረጋጋት እንዳይከተሰት ጥንቃቄ ይደረግ ዘንድ ተጠየቀ።
( ኢሳት ዜና ነሐሴ 11 ቀን 2010 ዓ/ም ) በድርጅቱ ውስጥ ያሉ የኢሳት ምንጮች እንደገለጹት ብአዴን በአሁኑ ወቅት በሁሉም ወረዳዎች የአመራር ለውጦችን እያደረገ ሲሆን፣ የለውጡ እንቅፋት ናቸው ተብለው የተለዮ ዋነኛ አመራሮቹንም ለመቀየር ዝግጅቶች አጠናቋል።
ከደሴ ከ30፣ከሀይቅ ከ30፣ከኮምቦልቻ ከ40 በላይ አመራሮች በአዲስ አመራሮች መተካታቸውን የገለጹት ምንጮች ይህ መተካካት በሁሉም ወረዳዎች እየቀጠለ እንደሚገኝ አመልክተዋል።
በኦቦ ለማ መገርሳ የሚመራው የኦሮሚያ ክልል መስተዳደር በሺህዎች የሚቆጠሩ ነባር አመራሮችን ማንሳቱን ተከትሎ በክልሉ ውስጥ አለመረጋጋት መከሰቱ ይታወሳል።
ለረብሻው ዋነኛው ምክንያቱም፤ የተባረሩት ነባር አመራሮች ከኩርፊያ በመነሳት እና በፈጸሙት ስህተት ላለመጠየቅ በሚል ለወጣቶች ገንዘብ እየከፈሉ በህገወጥ ተግባራት ላይ እንዲሰማሩ ማድረጋቸው እንደሆነ አቶ ለማ ተናግረው ነበር።
አሁንም ከብአዴን የሚባረሩ ነባር አመራሮች በአማራ ክልል ተመሣሳይ ህገ ወጥ ተግባራትን እንዳያስፋፉ ከፍተኛ ጥንቃቄ መደረግ አለበት ያሉት ምንጮች፣ በክልሉ አንዳንድ ቦታዎች ከወዲሁ እየተስተዋሉ ያሉ ተገቢ ያልሆኑ የወጣቶች እንቅስቃሴዎች ከወዲሁ ካልተገቱ ፣ ለነዚህ ተባራሪ ኃይሎች ሰፊ በር ሊከፍቱ ይችላሉ ሲሉ አስጠንቅቀዋል።
በሀርቡ እና በመርሳ ህዝቡ በአንድ በመሰባሰብ የራሱን ሰላም ለመጠበቅ ቃል መግባቱን ያደነቁት እነዚሁ ምንጮች፤ የሌላው አካባቢ ነዋሪም ከዚህ ትምህርት በመውሰድ የራሱን ሰላምና ጸጥታ በንቃት እንዲጠብቅ አሣስበዋል።